አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካን አገር ከሚገኘው አልባስተር ኢንተርናሽናል ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር በጨንቻ  ዙሪያ ወረዳና ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ቀበሌያት የተሰሩ የተለያዩ ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን መጋቢት 29/2017 / የዩኒቨርሲቲው፣ የጋሞ ዞንና የተለያዩ ወረዳዎች አመራሮች በተገኙበት አስመረቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ፕሮጀክቶቹ በጨንቻ ዙሪያ ወረዳና ከተማ አስተዳደር ሀይዞ ዶርዜ፣ ጺዳ ፣ ሻዬ እና ዶርዜ ጤና ጣቢያ የተሰሩ ሲሆን ከእንሰት ቃጫ እሴት የተጨመረባቸው የተለያዩ ጌጣ ጌጦች የሚመረቱበት ማዕከል፣  ዘመናዊ የእንሰት ማቀነባበሪያ ወፍጮ ቤትና የእናቶች ማቆያና የሴቶች የሽመና ማዕከል ተመርቀው ሥራ የጀመሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከእንሰት ድኅረ ምርት ሂደት ጋር ተያይዞ የሚከሰት የምርት ብክነትን፣ የጥራት እንዲሁም በሴቶች ላይ ያለውን ከፍተኛ የጉልበትና የጊዜ ጫና የሚያስቀሩ ቴክኖሎጂዎችን አበልጽጎ ለማኅበረሰቡ እያስተዋወቀ  የሚገኝ ሲሆን በዕለቱ የተመረቁ ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ከዚሁ ሥራ ጋር የተያያዙ ናቸው ብለዋል፡፡ በዕለቱ የተመረቁት ፕሮጀክቶች ዩኒቨርሲቲው አልባስተር ኢንተርናሽናል ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በትብብር ያሰራቸው መሆናቸውን ገልጸው ፕሮጀክቶቹ በተለይ ለሴቶችና ወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድልና ገቢ በመፍጠር ረገድ እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ጫናንና  የጊዜ ብክነትን በማስቀረት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡

የፕሮጀክት ምረቃ መርሃ ግብሩ የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ በዕለቱ በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ እያካሄደ ከሚገኘው የእንሰትና አፕል ንቅናቄ መድረክ ጋር የተገናኘ መሆኑ የተለየ ያደረገዋል ያሉት ዶ/ር ተክሉ ለንቅናቄው መሳካትም ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ተቋም የሚጠበቅበትን ይወጣል ብለዋል፡፡ ከበሽታ የጸዳ ችግኝ በስፋት ማግኘት ከእንሰት ጋር ተያይዘው ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል መሆኑን ያወሱት ም/ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው ከአልባስተር ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር በርካታ ከበሽታ የጸዱ የእንሰት ችግኞችን አባዝቶ ማቅረብ የሚችል የቲሹ ካልቸር ቴክኖሎጂ ማስገባቱንና ይህም ቴክኖሎጂ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ሥራ የሚጀምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር ደምስ አድማሱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን እየሰራ መሆኑ የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተመረቁት ፕሮጀክቶች በዘላቂነት ማኅበረሰቡን ማገልገል እንዲችሉ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ያሳሰቡት አስተዳዳሪው የዞኑ መንግሥት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የአልባስተር ኢንርናሽናል መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሻነን ፈርናንዶ ድርጅታቸው በገጠር ሴቶች ጤና፣ ምግብ ዋስትና፣ ሥራ ፈጠራና አቅም ግንባታ ላይ የሚሰራ መሆኑን ገልጸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተለይ የእንሰት ምርትን በማዘመን ከእንሰት ሴቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድልና ገቢ እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ የተመረቁት በሀይዞ ዶርዜ ከቃጫ የተለያዩ ጌጣ ጌጦች የሚመረቱበትና የሚሸጡበት ማዕከል፣ በዶርዜ ጤና ጣቢያ የተሰራው የእናቶች ማቆያ እንዲሁም በሻዬ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የእንሰት መፋቂያ ወፍጮ ቤት በዚህ ልክ አልቆና ሴቶች ተጠቃሚ ሲሆኑ በማየታቸው በእጅጉ እንደተደሰቱ ተናግረዋል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በመስራታችን ኩራት ይሰማናል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በቀጣይም መሰል  የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን መሥራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ የተመረቁት ፕሮጀክቶች ለ38 ሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በተለይ ሴቶች የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡ በሻየ ቀበሌ የተመረቀው የእንሰት መፍጫና መፋቂያ ወፍጮ ቤት እንደ ሀገር 34ኛው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ተጨማሪ ወፍጮ ቤቶችን ለማቋቋም ይሰራል ብለዋል፡፡ ከእንሰት ቃጫ የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን የሚያመርተው ማኅበር ምሩቱን እስከ አሜሪካን ድረስ በመላክ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ጭምር ማስገኘት የጀመረ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ  በመስኩ ዩኒቨርሲቲው ሥልጠና በመስጠት 5 ማኅበራትን ማደራጀቱንም አክለዋል፡፡

በዶርዜ ጤና ጣቢያ የተመረቀውን የእናቶች ማቆያ ማእከል ሥራ ያስተባበሩት በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተማራማሪ ምስጉን ሸዋንግዛው በበኩላቸው በጤና ተቋማት የሚገኙ የእናቶች ማቆያ ማዕከላት የወላድ እናቶችንና ሕጻናትን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸው በአብዛኛው እነዚህ ማዕከላት የግብአት ችግር ያላባቸውና ተገቢውን አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው፡፡ በጤና ጣቢያው የተሰራው የእናቶች ማቆያ ለእናቶች ምቹ ሆኖ የተሰራ ሲሆን በአስፈላጊ ግብአቶች እንዲሟላ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

 

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

 

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ /ቤት