የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንሰሳትና ዓሣ ኃብት ምርምር ማዕከል  ከሁለት መቶ ሺ በላይ የዳልጋ ከብቶች በጎሮርሳ በሽታ እንዳይጋለጡ ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት የቆየ ቅድመ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን ገልጿል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ክትባቱ በሽታው በታየባቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ጎፋና ጋርዱላ ዞኖች የተሰጠ ሲሆን በሥራው የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የዘርፉ መምህራንና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ተቋሙ ከመማር ማስተማርና ምርምር ተግባራት ባሻገር ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የክትባት ዘመቻው የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመግታት በቀረበ ጥያቄ መሠረት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ለክትባት መድኃኒት ግዥ ብቻ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ዩኒቨርሲቲው ወጪ ማደረጉን የገለጹት ዶ/ር ተክሉ በዘመቻው ጎሮርሳና አባ ጎርባ ለተሰኙ ሁለት በሽታዎች ክትባት አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ 

የማኅበረሰብ ጉድኝትና የኢንደስትሪ ትስሰር ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት በቅርቡ በአከባቢያችን የተከሰተውን የከብቶች በሽታ ተከትሎ እንደ ተቋም የተሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ዩኒቨርሲቲው ሁሌም ከማኅበረሰቡ ጎን መሆኑን ያሳየና ያረጋገጠ ነው፡፡ በሽታው እንደተከሰተ ዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎችን ለሁለት በማደራጀት ማሰማራቱን የገለጹት ዶ/ር ቶሌራ የመጀመሪያው ቡድን በሽታውን አስመልክቶ ጥናት የሚሰራ ሲሆን ሁለተኛው በድን የበሽታ መከላከያ ክትባት የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንሰሳትና ዓሳ ኃብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር  አቶ እሳቱ ፈቀደ የተከሰተው በሽታ በእጅጉ የእንስሳት ጤናን እንዲሁም ምርታማነትን የሚጎዳ በመሆኑ ምርምር ማዕከሉ ያሉትን ባለሙያዎች በመጠቀም በበሽታው ለተያዙ ከብቶች ሕክምና ላልተያዙ ደግሞ መከላከያ ክትባት በመስጠት ጉልህ ሚና መጫወት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በእንሰሳትና ዓሣ ሃብት ምርምር ማዕከል የእንሰሳት ጤና መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የቡድኑ አስተባባሪ ዶ/ር መስፍን ሹርቤ የጎሮርሳ በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው ሁለት መቶ ሺ ዶዝ ክትባት በመግዛት በተገቢው መንገድ ማሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ጤና ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ዋሲሁን ስዩም በተዋቀረው ቡድን የክትባት ዘርፍ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸው በክልሉ የዳልጋ ከብቶች ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ በሽታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ የዳልጋ ከብቶች ጎሮርሳ በሽታ ወረርሽኝ ጊዜውን ጠብቆ ክትባት የተሰጠ ባለመሆኑ ሊከሰት እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የእንስሳት ሕክምና መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ኤፍሬም ቶራ የተከሰተው ወረርሽኝ አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ በመሆኑ መሠረታዊ መረጃ በመሰብሰብ  መረጃ የመለዋወጥ ሥራ በጥናት ቡድኑ አማካኝነት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

 ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

 ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ /ቤት