አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶችን በማደራጀትና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ላበረከተው አስተዋጽኦ የዕውቅና እና በባልታና ጨንቻ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የቤተ ሙከራዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የጉብኝት መርሐ ግብር ከመጋቢት 25-26/2017 ዓ/ም ተካሂዷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ጉብኝቱ በትምህርት ቤቶቹ የተግባር ተኮር ትምህርት አሰጣጡን ለመገምገም፣ ዩኒቨርሲቲው በሰጠው ድጋፍ የተመዘገቡ ለውጦችን በመመልከት በቀጣይም ቅንጅታዊ አሠራሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ገልጸዋል፡፡ እንደ ሀገር በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ የማስተማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት እና የአመራር ጉድለት የተማሪዎች አፈጻጸም ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ድጋፍ በመታገዝ ት/ቤቶቹ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እያደረጉ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑንና ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ በበኩላቸው የሳይንስ ትምህርትን ጥራት ለማሳደግ እና ተማሪዎች ለአካዳሚክ ስኬት በሚገባ የታጠቁ እንዲሆኑ ኮሌጁ የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ እና የማስተማር ዘዴን የሚያሻሽሉ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በትምህርት ቤቶቹ የተደራጁት ቤተ ሙከራዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በዞኑ የትምህርት ጥራትና ውጤት ችግሮች አኳያ የሚታዩ ጉድለቶችን መቅረፍና ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት በመቅረጽ ከጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በተመረጡ 10 ወረዳዎች ባሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በ2015 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በኩል በዞኑ ባልታ፣ ጨንቻ፣ ምዕራብ አባያ እና ቦረዳ ወረዳዎች ባሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራ ቁሳቁስ የማደራጀትና ሙያዊ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር አዲሱ አዳሙ ባለፈው የትምህርት ዘመን ከ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት አንጻር ከዞኑ አጠቃላይ ተፈታኞች መካከል 5.5 በመቶው ብቻ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ማስመዝገባቸው ዘርፉ አስቸኳይ የተሐድሶ ሥራ እንደሚያስፈልገው የማንቂያና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ፍላጎትን አጉልቶ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ተቀናጅቶ መሥራት ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው እያበረከተ ላለው ድጋፍ አመስግነው ቅንጅታዊ አሠራሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የትምህርት ቤቶቹ ርእሳነ መምህራን፣ መምህራንና ባለሙያዎች ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችን ማምጣት የሚያስችል ቤተ ሙከራ የማደራጀት እና የሥልጠና ድጋፍ በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በተለይም በጨንቻ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በቤተ ሙከራ ውስጥ የነበሩ ቁሳቁሶችና ለዐሥር ዓመታት ያህል ያለአገልግሎት የቆዩ ኬሚካሎች ስጋት የተማሪዎችን የተግባር ትምህርት ማስተጓጎሉን አስታውሰው ኬሚካሎቹን በማስወገድና ከፊሉንም አሻሽሎ ወደ አገልግሎት በመመለስ በተሠራው ሥራ ትምህርት ቤቱ ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ ማትረፍ መቻሉን በአድናቆት ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከድጋፉ ባሻገር የመጣውን ለውጥ መከታተሉ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያነሳሳ መሆኑንም ተናግረዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ቤቶቹ የሳይንስ ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች እና ቁሳቁሶችን በዓይነት፣ በመጠን እና በባሕርይ በመለየት በአያያዛቸው ላይ ለሳይንስ መምህራን እና ለቤተ ሙከራ ረዳቶች ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲሁም ቤተ ሙከራዎችን መልሶ በማደራጀት በኩል የጎላ አስተዋጽኦ በማበርከቱ የዕውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡
ልኡኩ ከእነዚህም በተጨማሪ በካምባ እና ኤዞ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ ሙከራዎችን ጎብኝቷል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት