በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ሁለት ቀበሌያት ለሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ የተሻሻሉ የበግ ዝርያዎች ድጋፍ ትናንት መጋቢት 23/2017 ዓ/ም ተደርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ድጋፉ በጨንቻ ዙሪያና በዲታ ወረዳዎች በሚገኙ ስድስት ቀበሌያት በኮሌጁ እየተከናወነ የሚገኝ ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በእስከ አሁን ቆይታው በሁለቱ ወረዳዎች የሚገኙ 180 አርሶ አደሮችን በተሻሻሉ የዶሮና የበግ እንዲሁም በጓሮ አትክልት ዘርፎች ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡
በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የኮሌጁ የድኅረ-ምረቃ ትምህርት አስተባባሪ አቶ አግደው አበበ ድጋፉ በደጋማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሕይወት ለመቀየር የሚያስችል የግራንድ ምርምር ሥራ ውጤት አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው ለማኅበረሰቡ የቀረቡት የበግ ዝርያዎች የአካባቢውን የአየር ሁኔታ በቀላሉ በመላመድ ለእርባታ የተሻሉ ዝርያዎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ የቦንጋ የበግ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እሳቱ በቀለ በማዕከሉ ለተለያዩ የአየር ንብረቶች ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች የመለየትና በሂደትም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ ለአርሶ አደሮቹ የተሸጋገሩ የበግ ዝርያዎችም የዚሁ ሥራ አካል መሆናቸውን አቶ እሳቱ ጠቁመዋል፡፡
የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ሽፈራው ሽርጌ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ከዚህ ቀደም ለአካባቢው አርሶ አደሮች የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ለመሰል የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ቢቀጥል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት