የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ከጸረ ሙስናና ሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች መልካም ሥነ ምግባር፣ የዲስፕሊን ጥሰቶችና ሊወሰዱ የሚችሉ ቅጣቶችን አስመልክቶ ሚያዝያ 4/2017 ዓ/ም ለዋናው ግቢና ለሳውላ ካምፓስ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ም/ዲን ሳተናው ሳንዶ ከዚህ ቀደም የዲሲፕሊን መመሪያውን አስመልክቶ ገለጻ መደረጉን አስታውሰው በቅርብ ጊዜያት ከተከሰቱ የዲሲፕሊን ጥሰቶች አብዛኛው በአንደኛ ዓመት ተማሪዎች የተፈጸሙ በመሆኑ የቅጣት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት በድጋሚ ለማስተማር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ም/ዲኑ መመሪያው የመመገቢያ አዳራሽ፣ የመኝታ ክፍሎች፣ ክሊኒክ አካባቢ እና አጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከት ሲሆን በመኝታ ክፍሎች የማይፈቀዱ የኤሌክትሪክ መገልገያዎችን መጠቀም፣ ፍራሽና የትራስ ጨርቆችን መቅደድና መጣል፣ ዕቃዎችን ከክፍል ወደ ክፍል ማዘዋወር፣ በምግብ ዝግጅትና በመመገቢያ አካባቢ ያለፈቃድ መገኘት፣ በክሊኒክ አካባቢ ሕጋዊ ያልሆኑ ደረሰኞችን በማምጣት ያልተገባ ክፍያ መጠየቅ፣ በግቢው ውስጥ ሲንቀሳቀሱ በቡድን ሁከት መፍጠር እንዲሁም ድምፅ አልባ መሣሪያና አደንዛዥ ዕፅ ይዞ መገኘት በዲሲፕሊን ጥሰት ከሚያስቀጡ ድርጊቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ድርጊቶቹ ሲደጋገሙ ከቃል ማስጠንቀቂያ ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታ መገለል፣ ከዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ መባረር እንዲሁም በሀገሪቱ የትኛውም ዩኒቨርሲቲ እንዳይማሩ እስከማድረግ ድረስ የሚያስቀጡ መሆኑን ም/ዲኑ አብራርተዋል፡፡
የጸረ ሙስናና ሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሴፍ ወርቁ ተማሪዎች የዲሲፕሊን መመሪያውን በሚገባ ተረድተው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በጥሩ ሥነ ምግባር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ለመሰል የዲሲፕሊን ጥሰቶች ሳይጋለጡ የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲወጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ተሳታፊ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ከመድረኩ ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና በቆይታቸው ወቅት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት