አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአምዩ አዩሲ ፕሮጀክት አማካኝነት የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን መልሶ በማልማትና ሌሎች በፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየሆኑ በሚገኙ የማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ዙሪያ በትብብር መሥራት በሚቻልበት ሆኔታ ላይ ከጋሞ ዞን፣ ከአርባ ምንጭ እና ከገረሴ ከተማና ወረዳ አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

በዕለቱ በገረሴ ከተማ የተፈጠረን ከፍተኛ ጎርጅ መልሶ ለማልማት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀ ንድፈ ሃሳብና ዲዛይን ለውይይት ቀርቧል፡፡ 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ወደ ተግባር ሊቀየሩ የሚችሉ ምርምርን መሠረት ያደረጉ እውነተኛ ዕውቀት እንዲሁም መረጃ ማውጣት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ሥራ እንደመሆኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለይ በአምዩ አዩሲ ፕሮጀክት ሀገር ውስጥ ባሉ ግብአቶች ሊሰሩ የማይችሉ ምርምሮችን በማካሄድ ትልቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከምርምር ባሻገር ጫሞ ሐይቅን ከመታደግ አንጻር በርካታ ሥራዎችን በተለይ በገረሴና ዙሪያው ላይ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተክሉ በፕሮጀክቱ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ሰርቶ ማሳያ በመሆናቸው ሥራውን ይበልጥ ለማስፋት ከዞኑ፣ ከከተማና ወረዳ መዋቅር ጋር ይበልጥ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መሥራት በማስፈለጉ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን አውስተዋል፡፡

የአምዩ አዩሲ ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በአርባ ምንጭና አካባቢው የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብትና ሥነ-ምኅዳር በብዙ ያልተጠቀምንበት መሆኑን ተናግረው ይህንን ዕምቅ ሀብት የመጠበቅና የመንከባከብ ጉዳይ የዚህ ትውልድ ግዴታ ነው ብለዋል፡፡ የአምዩ አዩሲ ፕሮጀክት በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብትና ሥነ-ምኅዳር በዘላቂነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ጥናቶችን እያካሄደ ሲሆን በሁለተኛው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ የምርምር ውጤቶቹን ወደ መሬት የማውረድ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ከሚገኘው ደን 80 ከመቶ ያህሉ የጠፋ መሆኑ ሐይቁ ምን ያህል አደጋ ውስጥ እንዳለ ያሳያል ያሉት ዶ/ር ፋሲል በፕሮጀክቱ የተገኙ የምርምርና የተግባር ልምዶች ላይ ተመሥርቶ ከአካባቢው መንግሥት ጋር በቅንጅት መሥራት ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የምርምር ውጤቶቹ ላይ ተመሥርቶ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስና ረግረጋማ ስፍራዎች ላይ ውጤታማ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን በሙከራ ደረጃ ሰርቶ ማሳየት ችሏል ያሉት ዶ/ር ፋሲል በገረሴ ጌዣ ደን ውስጥ እንዲሁም በጫሞ ዳርቻ ላይ የተሰሩ የአፈርና ውኃ ጥበቃና መልሶ ማልማት ሥራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ትውልድ ጫሞን የማዳን ዕድል ያለው የመጨረሻው ትውልድ መሆኑንም ዶ/ር ፋሲል  በገለጻቸው አንስተዋል፡፡

በአምዩ አዩሲ ፕሮጀክት የንኡስ ፕሮጀክት 6 አባል የሆኑት ዶ/ር ስዩም ጌታነህ ባለፉት ዓመታት በገረሴና አካባቢው በተሰሩ ሥራዎች ቀላልና በአካባቢው የሚገኑ ግብአቶችን በመጠቀም ውጤታማ የአፍርና ውኃ ጥበቃ እንዲሁም ደንን የመጠበቅና መልሶ ማልማት ሥራ በማከናወን ሐይቁን ብሎም ተፈጥሮን ማዳን እንደሚቻል በተግባር መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከመልሶ ማልማት ሥራዎች በሻገር 8 ሄክታር ደን ማልማት መቻሉንም ዶ/ር ስዩም ጠቅሰዋል፡፡ የተግባር ሥራ የምንሰራበት ትክክለኛው ጊዜ ይህ ነው ያሉት ዶ/ር ስዩም ፕሮጀክቱ ከላይ ከተጠቀሱ ሥራዎች ባሻገር በገረሴ ኦሮ አካባቢ የአፕል ተክልን ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅ እንዲሁም የአግሮ ፎረስትሪ አሠራሮችን የማላመድ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ምርምር ላይ የተመሠረቱ በርካታ ማኅበረሰብ ተኮር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረው በአምዩ አዩሲ፣ በእንሰት፣ በታዳሽ ኃይል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ በእጅጉ ትብብር የሚፈልግ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ቶሌራ ከአከባቢው የመንግሥት መዋቅሮች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መሥራት መቻል ከዚህ በተሻለና በሰፋ መንገድ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በገረሴ ከተማ በመሬት መሸርሸር ምክንያት የተከሰተውን ከፍተኛ ጎርጅ መልሶ ለማልማት የተዘጋጀውን ዲዛይን ያቀረቡት ኢ/ር ጌትነት መለሰ በከተማው የተፈጠረው ጎርጅ በቶሎ አስፈላጊው የመልሶ ማልማትና የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ካልተሰራበት በከተማው ለሚገኙ ነዋሪዎች፣ ተቋማትና የመንገድ መሠረተ ልማት አደጋ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ቦታው እንዲያገግም ሙከራ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የተሰራው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ውጤታማ ባለመሆኑ ችግሩ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷልም ብለዋል፡፡ በመሆኑም የተፈጠረውን ጎርጅ እንዳይሰፋና ቦታው ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ የሚያስችል ሶስት አማራጮች ያሉት ዲዛይን በዩኒቨርሲቲው በኩል ተዘጋጅቶ መቅረቡን ኢ/ር ጌትነት ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀክሜ አየለ በሰጡት የማጠቃለያ ሃሳብ በዕለቱ ከቀረቡት ገለጻዎች ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲሁም የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን መልሶ ለማላመት የሚያስችል ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትልቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ ሐኪሜ ጫሞና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን እንዳናጣ በትኩረት መሥራት ይገባናል ብለዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጀመራቸውንና ፓይለት ያደረጋቸውን የመልሶ ማልማት ሥራዎች ማስፋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት አቶ ሐኪሜ በተለይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተሳትፎ በመጨመርና ከመንግሥት መዋቅር ጋር ያለን ቅንጅት በማጠናከር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ በሁሉም ዘርፍ ዩኒቨርሲቲው በሚሰራቸው ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ላይ ይበልጥ ተቀናጅቶና ተባብሮ ለመሥራት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ /ቤት