የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዴርማቶሎጂ ት/ክፍል ከትሮፒካል ሜድስን ኢንስቲትዩት (Institute of Tropical Medicine) ጋር በመተባበር በቦልቦ(Cutaneous leishmaniasis) ሕክምና ዙሪያ ከቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ ከጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች፣ ከዶርዜ ጤና ጣቢያና ከጨንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ኃላፊዎችና ከሌሎች የማኅበረሰብ አስተባባሪዎች ጋር የማኅበረሰቡ የቦልቦ ሕክምና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ውይይት ግንቦት 21/2017 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ዶ/ር ምህረት ተጫኔ በዩኒቨርሲቲው ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዴርማቶሎጂ ት/ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር፣ ተመራማሪና በአንትወርፕ ትሮፒካል ሜድስን ኢንስቲትዩት ሳንድዊች የፒ.ኤች.ዲ ተማሪ ሲሆኑ የውይይቱ ዓላማ በዘመናዊ የቦልቦ ሕክምና አጠቃቀም ዙሪያ የዶርዜ ጤና ጣቢያ፣ የጨንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት ለቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻዎች ማኅበረሰቡ ቦልቦን ጨምሮ የተዘነጉ የሐሩራማ አካባቢዎች በሽታዎችን ለመከላከል ዘመናዊ ሕክምናውን በተገቢ ሁኔታ እንዲጠቀምና በሽታዎቹን ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፍ እንዲያስተባብሩ ኃላፊነትና ኦረንቴሽን መስጠት ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ጠቅላላ ሆስፒታል ብቻ ዘመናዊ የቦልቦ ሕክምና ሲሰጥ የቆየ በመሆኑ አንድ የቦልቦ ታማሚ ሕክምናውን ለማግኘት አርባ ምንጭ መምጣትና ለአንድ ወር ያህል ጊዜ አልጋ መያዝ የሚጠበቅበት እንደመሆኑ ከኢኮኖሚያዊ አቅም ጋር ተያይዞ ታካሚዎች አገልግሎቱን እንደማያገኙ ታስቦ በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሕክምናው በሽታው በሚገኝባቸው ደጋማ አካባቢዎች አቅራቢያ በተለይ በዶርዜ ጤና ጣቢያና በጨንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባልተማከለ ሁኔታ ሕክምናው እንዲሰጥ መደረጉን ዶ/ር ምህረት ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የበሽታው መጠን ባይቀንስም ወደ ጤና ጣቢያውና ሆስፒታሉ መጥተው የሚታከሙ ታካሚዎች ቁጥር አነስተኛ ሆኖ በመቀጠሉ በሕክምና አገልግሎት ላይ እንቅፋት እየሆኑ የሚገኙ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ውጤታማ ትግበራዎች እንዲደረጉ ማነቃቃት፣ ግንዛቤ መፍጠርና ትክክለኛ ያልሆኑ ግንዛቤዎችን የማረም ሥራ መሥራት ማስፈለጉን ዶ/ር ምህረት ጠቁመዋል፡፡
ቦልቦ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር ግን በብዛት ፊትንና ሕጻናትን የሚያጠቃ፣ ዘላቂ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጠባሳ የሚያሳርፍ መጥፎ በሽታ በመሆኑ በተከሰተበት አጭር ጊዜ ውስጥ ታማሚው አስፈላጊውን ሕክምና ካላገኘ ዘላቂ ለሆነ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት በመዳረግ ለመገለልና መድልዖ እንደሚያጋልጥ ዶ/ር ምህረት አብራርተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ዘመናዊ ሕክምናውም ሰማንያ በመቶ ውጤታማ በመሆኑ በተጠቀሱት የጤና ማዕከላት በነጻ የሚሰጠውን ዘመናዊ ሕክምና በቅድሚያ እንዲያገኙ በተለይ ወላጆች ሕጻናትን በወቅቱ እንዲያሳክሙ ማኅበረሰቡን ማነቃቃትና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚጠበቅ ተመራማሪዋ በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አሁን ባለንበት ሁኔታ በዘመናዊ ሕክምና በማይድኑ የቦልቦ በሽታ ዝርያዎች ዙሪያ የሚደረጉ ተጨማሪ ምርምሮችም ውጤታማ ግኝት እንዲመጣባቸው ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ዶ/ር ምህረት ጠይቀዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ምህረት ገለጻ ቦልቦ ገዳይ በሽታም ሆነ አጣዳፊ ምልክት የሌለው በሽታ መሆኑና ተጠቂዎቹ ደግሞ በብዛት ሕጻናት መሆናቸው ማኅበረሰቡ ሕክምናውን ቸል እንዲል ሳያደርግ እንደማይቀር የሚገመት ሲሆን በሽታው ባይገድልም በተለይ የፊት መልክን በማበላሸት ለዘላቂ ጉዳት እንደሚዳርግ በቂ ግንዛቤ ካለመኖሩ ጋር ዝንጋቴው የተፈጠረ ሊሆን ስለሚችል የቦልቦ በሽታ ሁኔታ በሳምንታዊ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ሪፖርት ሥርዓት ውስጥ ገብቶ ማኅበረሰቡ ነጻ ሕክምናውን እንዲጠቀም መቀስቀስ ይገባል፡፡ ተመራማሪዋ አክለውም ማኅበረሰቡ በተለምዶ የሚጠቀማቸው ባህላዊ ሕክምናዎችን አስመልክቶ ቆዳ በመጥበስ ወይም በመቃጠል የሚሰጠው ሕክምና የማይሽር ጠባሳ የሚያሳርፍ ከመሆኑም በላይ ለተጨማሪ ኢንፌክሽን ሊያጋልጥ የሚችል በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
የዶርዜ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ጋሻዬ አንጃ በበኩላቸው ቦልቦ በሂርጶ፣ በቢላላ ና ሻይ፣ ቱቱሻ፣ ጌማ፣ ሻማና ሌሎች መሰል አከባቢዎች የተለመደ ሲሆን በሽታው በተለይ ዕድሜያቸው ከ3 -15 ዓመታት ባሉ ሕጻናት ላይ እያሳረፈ የሚገኘው ተጽዕኖ በጣም የሚያሳዝን ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊው የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻዎች በማኅበረሰብ ማነቃቃት ላይ ያለማሰለስ በመሥራት በሽታውን ለመከላከልና ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ አሳስበው በጽ/ቤታቸውም በኩል አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችና ሌሎቹም ባለድርሻዎች በበኩላቸው ለበሽታው መከላከል አስፈላጊውን ግዴታ ሁሉ በትጋት የሚወጡና በሳምንታዊ ዕቅዶቻቸው ውስጥ የበሽታውን ሁኔታ መረጃ የተመለከተ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ አረጋግጠዋል፡፡ ማኅበረሰቡም በዘመናዊ ሕክምና የማይድኑ የቦልቦ ዝርያዎችን አስመልክቶ የሚደረጉ ምርምሮችን እንዲደግፍና መረጃ በመስጠት እንዲተባበር እንዲሁም በባህላዊ ሕክምና ዙሪያም በቂ ጥንቃቄ እንዲደረግ በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚያከናውኑ ቃል ገብተዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት