የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ‹‹Improving the Observance of the Rights of Accused Persons and Criminal Investigation, Rights of Prisoners and the Treatment of Juvenile Delinquents in the Ethiopian Criminal Justice System: the Case of Gamo and Gofa Zones›› በሚል ርእስ ያከናወነው ግራንድ ጥናት ላይ ሰኔ 07/2017 ዓ/ም የማረጋገጫ ዐውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ ጥናቱ በመ/ር ዳግም ወንድሙ ዋና ተመራማሪነት እንዲሁም በመ/ር አብርሃም ክንፈ፣ መ/ርት ንግሥት ግርማ እና Dr. Sam Ponniah ተባባሪ ተመራማሪነት የተከናወነ ነው።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የሕግ ት/ቤት ዲን ተወካይ አቶ አብርሃም ክንፈ እንደገለጹት ት/ቤቱ ከመማር ማስተማር ሥራው ባሻገር የፍትሕ ሥርዓቱን ለማገዝ በምርምር የተደገፉ ሥራዎች እየሠራ ሲሆን ይህ ጥናትም የተጠርጣሪዎች አያያዝና የምርመራ ሂደት፣ የታራሚዎች አያያዝ እና ከሕግ ጋር የተጋጩ ሕፃናት አያያዝ ላይ በማተኮር በጋሞ እና ጎፋ ዞኖች የተመረጡ ስምንት ወረዳዎች ላይ ተከናውኗል፡፡
የጥናቱ ግኝቶች እና አንድምታዎቻቸው ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ግብረመልስ ለማግኘት እና ከውይይቱ የሚገኙ ሃሳቦችን በማካተት ጥናቱን ለማዳበር ዐውደ ጥናቱ መዘጋጀቱንም ተወካይ ዲኑ ተናግረዋል፡፡
አቶ አብርሃም ባቀረቡት የጥናት ግኝት በተመረጡት ወረዳዎች የተጠርጣሪዎች፣ የታራሚዎችና ከሕግ ጋር የተጋጩ ሕፃናት አያያዝ እና የምርመራ ሂደት ላይ የሚታዩ ችግሮች በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን የመፍትሔ ሃሳቦችም ተጠቁመዋል፡፡
የመርማሪ ፖሊሶች የዕውቀትና ክሂሎት ማነስ፣ በምርመራ ሂደት ጉልበት መጠቀም፣ ዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ዘዴዎች ሥራ ላይ አለመዋል፣ ተጠርጣሪ በሕግ ጥፋተኝነቱ ሳይረጋገጥ እንደ ወንጀለኛ መቁጠር፣ ተጠርጣሪዎች ክሳቸውን ሳያውቁ ለበርካታ ቀናት በእስር መቆየት፣ መንግሥት የሚያቀርባቸው የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን አለማግኘት፣ ከሕግ ጋር የተጋጩ ሕፃናት የሚያዙበትና የሚቆዩበት የተለየ መንገድ አለመኖር፣ ጣልቃ ገብነት፣ የፍትሕ አካላት አለመናበብ፣ የወንጀሎች ውስብስብነት እንዲሁም የበጀት እጥረት በጥናቱ ከተጠቀሱ ችግሮች መካከል ናቸው፡፡
ችግሮቹን ለመቅረፍ የመርማሪ ፖሊሶችና የዐቃቤያን ሕግ አቅም መገንባት፣ የፍትሕ አካላት በጋራ የሚሠሩበትን ማእቀፍ ማዘጋጀት፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና የመሳሰሉ ነጻ ተቋማትን ማሳተፍ እና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር በመፍትሔነት ከተቀመጡ ጥቆማዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከውይይቱ የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት በግኝቱ መሠረት በቀጣይ የጋራ መፍትሔ ለማበጀት እንሠራለን ያሉት ተወካይ ዲኑ ለዚህም ፕሮጀክቶች በመቅረጽ ከፍትሕ ተቋማቱ ባሻገር መንግሥታዊ ያልሆኑ ደጋፊና ረጂ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ም/ፕሬዝደንት አቶ አንዱዓለም አምባዬ በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ በሁሉም የፍትሕ ተቋማት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው መሰል ጥናቶች ሥራዎችን በጋራ በመሥራት ችግሮችን ለመቅረፍ በእጅጉ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡ ጥናቱ አስፈላጊ ሃሳቦችን በማከተት ሲጠናቀቅ የሪፎርሙ አካል ሆኖ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቤኔዘር ተረፈ የቀረበው ጥናት ነባራዊ ችግሮችን በግልጽና በዝርዝር ያሳየ መሆኑን ተናግረው ለዩኒቨርሲቲው፣ ለሕግ ት/ቤት እና በጥናቱ ለተሳተፉ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ባለንበት ጊዜ የዲጂታልም ሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ ጣልቃ ገብነት በፍትሕ አሰጣጥ ላይ ያለው ተፅዕኖ እና የሚዲያ አስተዳደር የጥናቱ አካል ሆኖ ቢካተት የሚል ጥቆማቸውንም ሰጥተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከክልሉና ከዞኖቹ የተለያዩ የፍትሕ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት የመጡ ኃላፊዎችና ባለሙዎች የተሳተፉ ሲሆን በጥናቱ ግኝት የተጠቆሙ ችግሮች በዓይነትና በስፋት ቢለያዩም በየአካባቢያቸው የሚታዩ መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ጥናቱን አስመልክቶ ጥያቄዎችና ቢካተቱ ያሏቸውን ሃሳቦች ያጋሩት ተሳታፊዎቹ ችግሮቹን በመቅረፍ ፍትሕን ለማስፈን በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት