አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአለም ዓቀፍ የደን ምርምር ማዕከል(CFOR) እና ከአግሮፎረስትሪ ጋር በመተባበር በደጋና ወይና ደጋ የአየር ጸባይ የሚለሙ ከውጭ ሃገር የመጡ ተባይና በሽታን መቋቋም የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያየ የግራርና የባህር ዛፍ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን በማባዛት ለምርምርና የዘር ምንጭ ለማድረግ በግርጫ የምርምር ማዕከልና በኦቾሎ ኦዶ ቀበሌ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ነሃሴ 14 2017 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል የተተከሉት የግራርና የባህርዛፍ ችግኞች ለምርምር የሚረዱና ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችግኞቹ ለማኅበረሰቡ ተጨማሪ የገቢ አማራጭ የሚፈጥሩ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዝደንቱ ሥራው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተካላ መርሐ ግብር አንድ አካል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ቀጣይ የሚኖሩ የምርምርና ክትትል ሥራ በጋራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶ/ር አብደላ አመላክተዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በሀራችን ውስን የግራርና የባህር ዛፍ ዝርያዎች ያሉ መሆናቸውንና እነዚህ ነባር ዝርያዎች በበሽታ እየተጠቁ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ተናግረው ከተተከሉት ዝርያዎች ተባይን የመቋቋም አቅም ያላቸውን በምርምር የመለየት ሥራ እንደሚሰራና የተሻሉ ዝርያዎች እንደ እናት ዛፍ ሆነው ለማህበረሰቡ እንደሚሰራጩና ለወደፊት ለሚደርገው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የዘር ምንጭ ሆነው እንዲያገለግሉ እንደሚደርግ አመላክተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የደን ምርምር ተቋም(CFOR) ተመራማሪ ዶ/ር አጌና አንጁሎ በሀገራችን የሚገኙት የግራርና የባህርዛፍ ዝርያዎች ውስንና በበሽታ የሚጠቁ መሆናቸውን ጠቅሰው በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ተባይንና በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው በተለያየ ሥነ-ምህዳር ሊባዙ የሚችሉ ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውንና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ከውጭ ሀገር የመጡ የተለያዩ የግራርና የባህርዛፍ ዝርያዎች ላይ ምርምር በማድረግ ለአርሶአደሩ የማሰራጨት ሥራ ላይ ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት አተኩሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ለሥነ-ምኅዳሩ ተሰማሚ ምርታማ ዝርዎችን የመለየት ሥራ እንዲሁም በሥነ-ህይወታዊ ዘዴ ተባይና በሽታን መከላከያ ላቦራቶሪ ማቋቋም የፕሮጀክቱ ቀጣይ ተግባር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የግርጫ ደጋ የፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና የምርምር ፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዘነበ መኮንን ዛፎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸው የተተከሉት ዝርያዎች የተራቆቱ መሬቶችን በደን በመሸፈን ለአከባቢ ጥበቃ ከመዋላቸው ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ አማራጭ የገቢ ምንጭ ለመሆን አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት