አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከበሽታ የጸዱ የእንሰት ችግኞችን በፍጥነትና በብዛት ማምረትና ማባዛት የሚችል የእጽዋት ቲሹ ካልቸር ቤተ-ሙከራ በዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ አቋቁሞ ሥራ አስጀምሯል፡፡ ላቦራቶሪው በሂደት የሙዝ፣ የድንች፣ የሸንኮራ አገዳ፣ አፕልን ጨምሮ ሌሎች ተፈላጊ እጽዋትን በስፋት አባዛቶ የማሰራጨት ዕቅድ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ትብብር / ፕሬዝደንት / ተክሉ ወጋየሁ የቲሹ ካልቸር ቴክኖሎጂ የእንስሳትም ሆነ እጽዋት ዝርያዎችን በብዛት በቤተ-ሙከራ ውስጥ በስፋት ማባዛት የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የዚህ ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ትልቅ እንድምታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡  አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለይ ከእንሰት ድኅረ ምረት አሰባሰብ ሂደት ጋር የተያያዙ ምርምርን መሠረት ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ወደ አርሶ አደሩ ማዳረስ የጀመረ መሆኑን የገለጹት / ተክሉ የዚህ ቤተ-ሙከራ መቋቋም አርሶ አደሩ ከበሽታ የጸዱ ችግኞችን በብዛት እንዲያገኝ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን  የሚያሳድግ እንዲሁም  ዩኒቨርሲቲው እንሰት ላይ የሚሰራውን ሥራ የተሟላ የሚያደርግ ነው ብለዋል። የዚህ ዓይነት ዘመኑን የዋጁና ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ የሚጠቅሙ  ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ መቻል እንደ ተቋም ትልቅ ስኬት መሆኑንም / ተክሉ አንስተዋል።

በቲሹ ካልቸር ቴክኖሎጂ የሚባዙ ችግኞች በገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ሲሆን  ይህም እንደ ተቋም ትኩረት የተሰጠበትን  የምርምር ኮሜርሻላይዜሽን ጽንሰ ሃሳብን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን /ፕሬዝደንቱ አብራርተዋል። ቴክኖሎጂው ዩኒቨርሲቲው ከምርምር ባሻገር ከፍተኛ ገቢ የሚያገኝበትን አማራጭ የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ላቦራቶሪው ሥራ በጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ተቋማትና ባለሀብቶች የተለያዩ የእህል ዝርያዎችን አንድናባዛላቸው ጥያቄ እያቀርቡ ነው ያሉት / ተክሉ ዩኒቨርሲቲው  ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ቤተ-ሙከራው  ከዚህ በላይ ሰፍቶና ዘምኖ እንዲሠራ ተጨማሪ ግብአቶች እንዲሟሉለት ይደረጋል ብለዋል።

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን / ደግፌ አሰፋ ቤተ-ሙከራው በአብዛኛው በኮሌጁ የነበሩ ግብአቶችን በመጠቀም የተደራጀ መሆኑን ገልጸው እንደ ኮሌጅ የዚህ ዓይነት አድቫንስድ ቤት ሙከራ ባለቤት መሆን ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።  የቤተ-ሙከራውን ስታንዳርድና ስፋት ከፍ የማድረግ ጉዳይ በቀጣይ በትኩረት የሚሰራበት መሆኑን የገለጹት / ደግፌ በዕቅዳችን ልክ መስራት ከቻልን የአካባቢውን አርሶአደሮች ብሎም የሌሎች ተቋማትን የዘር ወይም ችግኝ አቅርቦት ማሟላት እንችላለን ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት አማካሪና በኮሌጅ የእጽዋት ማዳቀልና የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ / መሠረት ፈንታ የቲሹ ካልቸር ቴክኖሎጂ ያለምንም የጊዜ ገደብ ዓመቱን ሙሉ ከበሽታ የጸዱ የእጽዋት ችግኞችን / Planting Materials/ / በእጅግ ከፍተኛ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማባዛት የሚችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸዋል። ቤተ- ሙከራዉ ሲመሠረት አስፈላጊውን ስንታንዳርድ በጠበቀ መንገድ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል ያሉት / መሠረት ቤተ ሙከራው በሙሉ አቅሙ መስራት የሚችልበት ሁኔታ ከተፈጠር ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ገቢ የሚያገኝበት ዘርፍ እንደሚሆን እመነታቸውን ገልጸዋል።

 

በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የሆርቲካልቸር መምህርና ተመራማሪ / ሳቡራ ሻራ ከበሽታ የጸዳ ችግኝ ማግኘት አለመቻል  የእንሰት ምርትና ምርታማነትን በእጅጉ እየጎዳ የሚገኘው የእንሰት አጠውልግ በሽታ  ዋነኛ መንስኤ መሆኑ በጥናታቸው መለየታቸውን ገልጸዋል። ንጹህና ከበሽታ የጸዳ ችግኝ አርሶ አደሩ እንዲያገኝ ማድረግ በጥናታቸው ካስቀመጧቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል እንደነበረም / ሳቡራ  አስታውሰዋል። በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው የእጽዋት ቲሹ ካልቸር ቤተ-ሙከራ በዋናነት ከበሽታ የጸዱ የእንስት ችግኞችን በብዛት ለአርሶ አደሩ ማደረስን ዓላማ ያደረገ መሆኑን የገለጹት / ሳቡራ ይህም  በበሽታው ምክንያት በእንሰት ላይ ሲከሰት የቆየውን የምርታማነት መቀነስ ችግር የሚቀርፍ ነው ብለዋል። በቤተ-ሙከራው መቋቋም ሂደት ውስጥ አሜሪካን ሀገር የሚገኘው አልባስተር ኢንተርናሽናል ከፍተኛ ሚና የነበረው መሆኑን ያወሱት ተመራማሪው  ወደፊት ቤት ሙከራዉ ከእንሰት ውጪ ያሉ የእህል ዘሮችን በዚሁ ቴክኖሎጂ አባዛቶ የማሰራጨት ዕቅድ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

በኮሌጁ የሆርቲካልቸር መምህርና ተመራማሪ / ገዛኸኝ ጋሮ በበኩላቸው በቲሹ ካልቸር የተባዛ ችግኝ ወይም ዘር የምረት አቅሙ ከፍተኛ ሲሆን ይህም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል። በቲሹ ካልቸር ዘር ማባዛት በከፍተኛ ሁኔታ ጊዜን፣ ገንዘብ እና ጉልበት ይቆጥባል ያሉት / ገዛኸኝ ከአንድ እጽዋት 10 ግራም የማይሞላ የእጽዋት አካል በውስድ ከአንዱ ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ በትንሹ እስከ አንድ ሺህ ችግኝ ማግኘት የሚያስችል አሠራር መሆኑንም አክለዋል። በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት ቲቪ ካልቸር ቤተ-ሙከራ ተመሰረቶ ሥራ መጀመሩ ለአካባቢው የግብርና ዘርፍ  መሻሻል በጎ አስተዋጽዖ ማበርከት የሚችል መሆኑንም አስረድተዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ /ቤት