በሀገራችን ከሚገኙ አንጋፋና ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሆኖ ከተመሠረተበት 1979 ዓ/ም ጀምሮ ከ84 ሺህ በላይ ብቁ ምሁራንን በመፍራት ለሀገራችን የሰው ሀብት ልማት የበኩሉን እየተወጣ ያለ አንጋፋ እና ሰመ ጥር ተቋም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆኑ ከተለዩ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባሉት ስድስት ካምፓሶች ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ በርካታ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑ በሳውላ ካምፓስ የ3ኛ ዓመት የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ተማሪ የሆነችው ተማሪ ባንቺጊዜ ደርብ በቲክቶክ ድህረ-ገጿ ላይ ባሰራጨችው ያልተገባ መልዕክት ምክንያት ምንም እንኳ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስከትል ቢሆንም አንዳንድ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት አንድ ዓመት እንድትታገድና ሌሎችም ከዚህ ተምረው እራሳቸው ካልተገባ ነገር እንዲታቀቡና ትምህርታቸው ላይ አተኩረው ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው፣ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ግብረ ገብነት በተሞላበት ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ይማሩ ዘንድ ለማስገንዘብ የተወሰደባትን የዲሲፕሊን እርምጃ መነሻ በማድረግ የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዩኒቨርሲቲውን አጀንዳ እያደረጉ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የሚስተዋለውን የመረጃ ክፍታት በመገንዘብ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሰው ሀሳቡን በነጸነት የመግለጽ መብት ያለው መሆኑ በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችም ሆነ በሀገራችን ሕጎች በተለይ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29 በሚገባ ተብራርቶ ይገኛል፡፡ ይህ መብት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችን የሚጨምር ቢሆንም ገደብ የሌለው (Absolute Right) ግን አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6 እና 7) በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች በሌሎች ሕጎች ሊገደብ የሚችል መብት መሆኑ በግልጽ ተመላክቷል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ 1152/2019 አንቀጽ 39(1) ተማሪዎች በመማሪያ ክፍላቸው የመገኘትና ትምህርታቸውን በሚገባ የመከታተል እንዲሁም የአካዳሚክ ሠራተኞች ከመማር ማስተማር ጋር በተያያዘ የሚሰጡትን ትዕዛዝ የማክበር ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል መምህራን ደግሞ ለሚያስተምሩት መርሃ-ግብር የተዘጋጀውን ሥርዓተ-ትምህርት መሠረት በማድረግ፣ የሀገሪቱን ሕግ፣ የተቋሙን ተልእኮና እሴት አክብሮ የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ የተማሪ-መምህር መብትና ግዴታ የመማር ማስተማሩ ስበት-ማዕከል እና ማናቸውም ያለአግባብ ሊያልፉት የማይገባ ቀይ መስመር ነው፡፡ ከዚህ አፈንግጦ የተገኘ መምህርም ሆነ ተማሪ እንደ አግባብነቱ በዲሲፕሊን፣ በአስተዳደራዊ እርምጃ፣ በወንጀል እና/ወይም በፍትሐ ብሔር ተጠያቂ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ 

የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የዲሲፕሊን መመሪያም መምህር የመማር ማስተማሩን ሂደት የመምራትና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ሲወጣ ተማሪዎች ደግሞ ህግ የማክበር እና የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞችን ከማንጓጠጥና ያልተገባ ንግግር ከመናገር መቆጠብ ይኖርባቸዋል ሲል አንቀጽ 7(6) እና አንቀጽ 6(12) ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ወደ ጎን በማለት ጥፋት ፈጽሞ የተገኘ እና በተቋሙ አካዳሚያዊ ሥራ ውስጥ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ካለ ከአንድ ወሰነ-ትምህርት እስከ ሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታ ሊታገድ እንደሚችል አንቀጽ 13(1፣1.6) ላይ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ በተጨማሪም አንድ ተማሪ ምንም አይነት መረጃ በሌለበት በአሉባልታና በመሰለኝ የመምህራንን ክብር መንካትና መሰል ተግባራትን መፈጸም እንዲሁም መምህራንን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ የሥራ ተነሳሽነትና ሞራል ሊጎዳ የሚችል ኃይለ ቃል መናገር፣ እንቅስቃሴን ማሰራጨት ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ በመመሪያው አንቀጽ 13(2)፣ 13 (2.10) እና 13(2.26) በማያሻማ ሁኔታ ተካቷል፡፡ 

ከላይ የተመለከቱ ድንጋጌዎች ከብዙ ጥቂቶቹ ሲሆኑ የዲስፕሊን ቅጣቱ የተላለፈባት ተማሪ አስባና አቅዳ ትውልድ ለመቅረጽ በሚተጉ መምህራን ላይ ስላቅ በሚመስል አነጋገር፤ ሥነ-ምግባር በጎደለው መልኩ የጠቅላላ ተማሪዎች ሃሳብ በማስመሰል “… እኛ ከ30 ደቂቃ በላይ እየሰማናችሁ ስላልሆነ፤ 30 ደቂቃ እንደሞላ እኛ መስማት ስለምናቆም፤ ከ30 ደቂቃ በኋላ ያለውን ጊዜያችሁን አታባክኑ፤ ሌላ የምትሠሩት ሥራ ካለ ውጡና ሂዱ፤ ተማሪው ከ30 ደቂቃ በኋላ እናንተን ማየትም፣ ማዳመጥም አቁሟል……” የሚል መልዕክት አጋርታለች፡፡ የተማሪዋ ንግግር የግል ፍላጎቷ ቢሆንም ሌሎች ተማሪዎችን ሊያነሣሣ በሚችል አኳኋን መሆኑ ጥፋቱን ከባድ ያደርገዋል፡፡

በተማሪዋ የተፈጸመው ጥፋት በተቋሙ፣ በሠራተኞችና በተማሪዎች መደበኛ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር፣ የተቋሙ ሠራተኞች (መምህራን) ክብር የሚነካ ብሎም ዩኒቨርሲቲውን የሚጎዳ ተግባር መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ በመሆኑም የተማሪዋ ድርጊት በወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል መሆኑ እንዳለ ሆኖ በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ዲሲፒሊን መመሪያ አንቀጽ 13 (2.10) እና 13(2.26) መሰረት እንኳ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት የሚያስቀጣ ድርጊት ነው፡፡  

ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው በተማሪዋ ላይ የወሰደው እርምጃ ከላይ የተዘረዘሩ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ መሆኑንን እንገልጻለን፡፡ ይሁን እንጂ ተማሪዋ የተወሰደባት የዲሲፕሊን እርምጃ ተገቢ አይደለም ብላ ካለች እንኳ በስነ-ስርዓት አግባብነት ባለው መንገድ ይግባኝ የመጠየቅ መብት ያላት መሆኑ እየታወቀ ያለአግባብ ከትምህርት እንደተባረረች በማስመሰል ያልተገባ ዝና ለማግኘት በማኅበራዊ ሚዲያ መልእክቶችን በማጋራት የዩኒቨርሲቲውን ስም በአሉታዊ መንገድ እንዲነሣ ከማድረግ እንድትቆጠብ እናሳውቃለን፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎችም ለሀገር ዕድገት በተለይ በመማር ማስተማር ምሁራንን በማፍራት እንድሁም በጥናትና ምርምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለን አንጋፋና ስመ ጥር ተቋም ያለበቂ መረጃ አጀንዳ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት