የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአገልግሎት ክፍል ኃላፊዎችና የጥራት ተጠሪዎች ከየካቲት 3-5/2018 ዓ/ም የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርትና አገልግሎቶ ጥራት ማሻሻያና ኢኖቬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር ረ/ፕ ስንታየሁ አበበ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ከተመረቀበት 2016 ዓ/ም ጀምሮ በየጊዜው እያደጉ የሚሄዱ አገልግሎቶችን እየሰጠ የቆየ ሲሆን በቅርቡም የተኝቶ ሕክምና አገልግሎት በመጀመር በሙሉ አቅሙ እየሠራ ነው።
አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ከዚህ ቀደም በተለይም የምርመራ ጥራትና የፅኑ ሕሙማን ሕክምናን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥልጠናዎች በጤና ሚኒስቴር መሰጠታቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ የአሁኑ ሥልጠናም የአገልግሎት ሰጪዎቹን ግንዛቤ በማሳደግ የሆስፒታሉን ሙሉ አገልግሎቶች ጥራት ለማስጠበቅና ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ ነው።
በሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስትና የሕክምና ጥራት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ባቡሎ በጤናው ዘርፍ አሁን ላይ ጥራትን መሠረት ያደረገ የሕክምና አገልግሎት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ግዙፍ የትምህርትና የሕክምና ተቋም ከመሆኑ ባሻገር የሆስፒታል ቱሪዝም ማእከል ለመሆን ከማለሙ አንጻር በእያንዳንዱ ክፍል የሚሰጠው አገልግሎት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። ጥራትን ለማስጠበቅ የሰው ኃይልን ማብቃት አንዱ መሣሪያ እንደመሆኑ ሥልጠናው ግንዛቤን በማሳደግ ሆስፒታሉን በጥራት መሠረት ላይ ለማቆም ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ዶ/ር ጌታቸው ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር ሜዲካል አገልግሎት ዘርፍ የሆስፒታል እና ዲያግኖስቲክ ኤክስፐርት የሆኑት አሠልጣኝ ደሳለኝ ባይሳ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት የአሠራር ማሻሻያዎችን በማውጣት ሲተገብር መቆየቱን ጠቅሰው ማሻሻያዎቹ በሆስፒታሎች የአመራር ሥርዓቱን ለማሳደግና ለማጠናከር፣ የአገልግሎት ጥራትና የታካሚ እርካታን ለማሳደግ ብሎም በጤና ተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት ወጥነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ እንደሚረዱ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል አዲስ እንደመሆኑና ሰፊ ተደራሽነትን ታሳቢ አድርጎ እንደመቋቋሙ አገልግሎት ሰጪዎቹ በሪፎርሞቹ ላይ በቂ ግንዛቤ ጨብጠው ጥራት ያለው ሕክምና መስጠት እንዲቻል ሥልጠናው መዘጋጀቱን አሠልጣኙ ተናግረዋል። ሥልጠናው በተመላላሽና ተኝቶ ሕክምና፣ በመድኃኒት አቅርቦት፣ ላቦራቶሪ፣ ፋይናንስ፣ የሰው ኃይልና የሕክምና ቁሳቁሶች አጠቃቀም፣ የተገልጋይ አቀባበልና ሌሎችም ላይ ያሉ ማሻሻያዎችና ኢኒሼቲቮችን አስመልክቶ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነውም ብለዋል።
ሌላኛዋ አሠልጣኝ በሚኒስቴሩ የ "SaLTS/Saving Lives Through Safe Surgery" ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ ሲስተር እታፈራሁ ዓላማው እንደተናገሩት ሥልጠናው 21 ምዕራፎች ያሉት የኢትዮጵያ የሆስፒታል አገልግሎቶች ማሻሻያ መመሪያ (Ethiopian Hospital Services Improvement Guideline/EHSIG) የሚተገበሩበት ስታንዳርዶችን ያካተተ ሲሆን በሆስፒታሉ ወጥነት ያለው፣ ጥራቱን የጠበቀና መስፈርቱን የሚያሟላ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ነው።
ሥልጠናውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ከሰጡ ሠልጣኞች መካከል የድንገተኛ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ምስክር ወ/ኪዳን ሕክምና የሁሉንም ክፍሎች ቀልጣፋ የጋራ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው ሥልጠናው በየአገልግሎት ክፍሎቻችን ያሉ ስታንዳርዶችን ተረድተን በሚገባ እንድንተገብርና ታካሚው ሳይጉላላ ጥራት ያለው ሕክምና እንዲያገኝ ሰፊ ዕውቀት ያስጨበጠን ነው ብለዋል።
ሌላኛው ሠልጣኝ በሆስፒታሉ የፋርማሲ ትምህርትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተወካይና የፋርማሲካል ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት አስተባባሪ አቶ አይኖሼ አዲዮ ሥልጠናው ነባሩን ዕውቀት የሚያዳብርና ከአዳዲስ ስታንዳርዶችና ኢኒሼቲቮች ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። ከሥልጠናው ያገኘነውን ግብአት ተግባራዊ በማድረግ ለታካሚዎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንሠራለንም ብለዋል።
በሆስፒታሉ የግዢ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ሠልጣኝ ደጀኔ ቶማስ በበኩላቸው በሆስፒታሉ የሕክምና አገልግሎት በአግባቡ እንዲከናወን የሚፈጸሙ ግዢዎች በተለይም የሕክምና ቁሳቁሶች በጥንቃቄና በጥራት መቅረብ ያለባቸው እንደመሆኑ ሥልጠናው ይህን አስመልክቶ ያሉ አሠራሮች ላይ ዕውቀት ያገኙበት መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





