የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከዓለም አቀፉ LM International ድርጅት ጋር በመተባበር በቦረና ዞን ሲያካሂድ የቆየውን "የገጸ-ምድርና የከርሰ-ምድር ውሃ አቅም እና ጥራት ጥናት" (Study of Surface and Groundwater Potential and Quality) የግምገማ አውደ ጥናት ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም አካሂዷል። በመድረኩ ላይ የጥናቱን ሂደትና ግኝቶች የሚገመግሙ ባለድርሻ አካላትና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ግምገማ ማካሄድ ሳይንሳዊ የምርምር ሂደት አንዱና ዋነኛው አካል መሆኑን ገልጸዋል። ቦረና ዞን ባላት ልዩ የአየር ጠባይና ሥነ-ምህዳራዊ አቀማመጥ ምክንያት የውሃ ሃብት አስተዳደር ላይ ተከታታይ ተጽዕኖዎችን ስታስተናግድ መቆየቷን የጠቀሱት ም/ፕሬዝዳንቱ፣ ጥናቱ ለውሃ ሃብት አስተዳዳሪዎችና ለፖሊሲ አውጪዎች እንደ ወሳኝ የመረጃ ምንጭ እንደሚያገለግል አብራርተዋል። ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ-ገዝ (Autonomous) ተቋምነት እየተሸጋገረ ባለበት ወቅት፣ መሰል ዓለም አቀፍ ትብብሮች ምርጫ ሳይሆኑ ተቋማዊ ግዴታዎች መሆናቸውንና አጋር አካላትን ለመቀበል ሁልጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰሜ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱን LM International በባለቤትነት የሚመራው ሲሆን ተቋሙ ደግሞ ከፍተኛ ሙያዊ የማማከርና የሳይንሳዊ ድጋፍ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህ የትብብር ፕሮጀክት በአካባቢው ያሉ የውሃ ጉድጓዶችን በሳይንሳዊ መንገድ ለማከም እንዲሁም የተቆፈሩ የውሃ አካላት ቀጣይነትና ዘላቂነት እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። በጥናቱ ሂደት የታዩ ጠንካራ ጎኖችና የተነሱ ገንቢ አስተያየቶች ተካተውበት፣ የተሟላ ሰነድ በቀጣይ ለባለድርሻ አካላት እንደሚቀርብም ጠቁመዋል።
በLM International ፕሮግራም ማኔጀር አቶ እሸቱ ጥላሁን፣ ድርጅቱ ለዚህ የጥናት ፕሮጀክት ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አስታውቀዋል። መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት መሰል ጥናቶችን ከቢሮ መደርደሪያ ባለፈ ወደ ተግባር በመቀየር የማህበረሰቡን የውሃ ችግር በዘላቂነት እንዲፈቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በLM International ከፍተኛ የWASH አማካሪ የሆኑት ሚስተር Mr Vonatan Stromgren፣ በቦረና አካባቢ ያለው መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ ካለመቀመጡ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር የሚስተዋሉ የጂኦሎጂ እና የሃይድሮሎጂ ውስብስብ ሂደቶች ፈታኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ ብቁ የዘርፉ ሙያተኞችን በመጠቀም እነዚህን ችግሮች መለየት እንደሚቻል ገልጸው፣ ጥናቱ ለዞኑ ውሃ ቢሮና በመስኩ ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች እንደ መመሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ አስተባባሪና ተመራማሪ ዶ/ር ደመላሽ ወንድማገኝ፣ ጥናቱ በዞኑ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። ጥናቱ የከርሰ-ምድርና የገጸ-ምድር ውሃን መጠን፣ የመቆፈር አቅምን፣ የሚገኘውን የመጠጥ ውሃ መጠን እንዲሁም ለሰው፣ ለከብቶችና ለግብርና ያለውን ጠቀሜታ በዝርዝር የዳሰሰ መረጃ መያዙን አስረድተዋል። የውሃው ጥራት ለተለያዩ አገልግሎቶች ያለውን ብቁነት የሚገመግሙ ትንታኔዎች ተካተውበት ጥናቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እንደሚረከብም አመላክተዋል።
መጨረሻም የቦረና ዞን ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሲኒየር ሃይድሮሎጂስት አቶ ሁሴን ገልገሎ፣ ጥናቱ በዞኑ ያለውን የመረጃ ክፍተት በመሙላት ረገድ ያለውን ጉልህ ድርሻ ገልጸው፣ በቀጣይም በሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ላይ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት


