አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮና ከጋሞ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር የክልሉን ቋንቋዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር ያለመ ለቋንቋ ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች ከሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው የመጀመሪያ ዙር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተጠናቀቀ። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ ክልሉ የበርካታ እሴቶችና ቋንቋዎች ጸጋ ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እነዚህን እሴቶች በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የሚወጣውን ተልዕኮ በማድነቅ ቋንቋን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር ክልሉ በእድገት ጎዳና ላይ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር አቶ ታፈሰ ዋልኤ ማዕከሉ የማኅበረሰቡ ባህልና ቋንቋ፣ ሀገር በቀል እውቀቶች እንዲሁም ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲቆዩ በቂ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ አነስተኛ ተናጋሪ ያላቸውና የመጥፋት አደጋ በተጋረጠባቸው በደቡብ ኦሞ ዞን የኦንጎታ፣ ኮይጉ እና ኤርቦሬ ቋንቋዎችን ለመታደግ ከተደረገው ጥረት ጎንለጎን የማኀበረሰቡ ባህላዊ የሰላም እሴቶች የሆኑትን የጋሞ "ድቡሻ ወጋን" እና የጋርዱላ ህዝቦች "ፊላ ጨዋታን" በዓለም ቅርስ መዝገብ (UNESCO) ለማስመዝገብ ሰፊ የምርምርና የሰነድ ዝግጅት ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ ቋንቋን በተሻለ ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ተመራጭ መሆኑን የገለጹት አቶ ታፈሰ፣ በመጀመሪያው ዙር የጋሞ፣ ዘይዜ፣ ጊዲቾ እንዲሁም ኮንሶና ደራሼ ቋንቋዎችን በአንድ ቴክኖሎጂ ቋት ለማስተሳሰር የባለሙያዎችን የመረጃ አሰባሰብ አቅም ማጎልበት የዚሁ ግዙፍ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ቋንቋዎች ዲጂታላይዜሽን ስነዳ አስተባባሪ አቶ ዋለልኝ በላይነህ በበኩላቸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት ዓመታት ብዝሃ ቋንቋ ልማት ስራዎችን በቴክኖሎጅ ተደራሽ ለማድረግ የወላይታ፣ አኝዋክ፣ ኑዌር፣ ማጃንግ እና ጉሙዝ ቋንቋዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ከወላይታ፣ አሶሳ እና ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲሰራ መቆየቱንና የአሁኑም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚሰራ ተመሳሳይ ስራ መሆኑን አብራርተዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ህንዳዊው ዶ/ር ሼከር ካሙኑሪ የዩኔስኮን (UNESCO) ጥናት በመጥቀስ እንደገለጹት፤ አንድ ቋንቋ በሌላ አብላጫ ተናጋሪ ባለው ቋንቋ የመዋጥና የመጥፋት እድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም በዓለም ላይ ካሉ 7,000 ቋንቋዎች መካከል እስካሁን በቴክኖሎጂው ዓለም (በጎግል ጭምር) እውቅና ያገኙት 2,00ዎቹ ብቻ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ያሏትን ከ80 በላይ ቋንቋዎች በቴክኖሎጂ በማስተሳሰርና የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025-2030" ራዕይን እውን ለማድረግ የድምፅ መረጃ ቋቶችን፣ የሞባይል መተግበሪያዎችንና ሶፍትዌሮችን የማበልጸግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ይህ ጥረትም አብላጫዎቹን የሀገሪቱ ቋንቋዎች ከዘመናዊው ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ኢትዮጵያን በዘርፉ ከዓለም ቀዳሚ እንደሚያደርጋት ዶ/ር ሼከር አብራርተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ዶ/ር ሳሙኤል ጎንደሬ እና ዶ/ር ሚልክያስ ዳርዛ እንደገለጹት፤ ስልጠናው ቋንቋዎቹን ከማሳደግ ባለፈ ለትምህርትና ለምርምር ሥራዎች ጠቃሚ ማጣቀሻዎችን ለማዘጋጀት ያስችላል። ስልጠናው በተለይም በስድስት ቋንቋዎች (ጋሞ፣ ዘይዜ፣ ጊዲቾ፣ ኮንሶ እና ደራሼ) ላይ ትኩረት አድርጎ ተውላጠ ስሞችን፣ የንግግር ድምፆችን፣ የቃላት ትርጓሜዎችን እና ሌሎች መዋቅራዊ ቅርጾችን በዲጂታል ዘዴ የመሰብሰብና የማደራጀት ሥራ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት


