አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 27 ቀን 2019 ዓ.ም (AMU) — በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት "Enset for Food Security and Climate Resilience" (እንሰት ለምግብ ዋስትና እና ለአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም) በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው 3ኛው ዓለም አቀፍ የእንሰት ምርምር ሲምፖዚየም ተጠናቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ይህ ዓለም አቀፍ አውደ-ጥናት ከአዩዳ ኤን አክሲዮን (Ayuda en Acción)፣ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ከዓለም አቀፍ የጄኔቲክ ኢንጂነሪንግ እና ባዮቴክኖሎጂ ማዕከል (ICGEB)፣ ከዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (Danida) እና ከሉሲ እንሰት (Lucy Enset) ጋር በመተባበር የተሰናዳ ሲሆን፤ በሁለቱ ቀናት ቆይታው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ እንግዶች፣ ተመራማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት 14 የምርምር ሥራዎች ቀርበዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የዘንድሮው ሲምፖዚየም የተካሄደው የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በእንሰት ምርምርና ፈጠራ ባስመዘገቡት የላቀ ውጤት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የ2026 ስኬት አዋርድ (FAO Achievement Award 2026) መቀበላቸውን ተከትሎ መሆኑ መድረኩን ታሪካዊና ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ፕሬዝደንቱ አያይዘውም ይህ ዓለም አቀፋዊ እውቅና የዩኒቨርሲቲውን ተመራማሪዎች ሳይንሳዊ ልህቀት፣ ቁርጠኝነት እና የፈጠራ አቅም በግልጽ እንደሚያሳይ ጠቁመዋል። እንዲሁም እንሰት ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም በደቡብ አካባቢዎች ለሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብና የኑሮ ዋስትና የሆነ፣ ድርቅን የመቋቋም ልዩ አቅም ያለው ሀገር በቀል እፅዋት መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው ለአካዳሚክ ሕትመት ብቻ ሳይወሰን ምርምሮቹን ወደ መሬት በማውረድ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የምርምር እና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው እንሰትን ለተቋማዊ ምርምር እና ፈጠራ ዋና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አድርጎ በመውሰድ በአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም፣ በበሽታ አስተዳደር፣ በማቀነባበር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኮሜርሻላይዜሽን (Commercialization) ላይ ጠንካራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ይህን መሰል ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ማስተናገድ ደግሞ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ምርጥ አእምሮዎችን በማሰባሰብ የዚህን ወሳኝ ሀገር በቀል ሀብት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን አመላክተዋል። ዶ/ር ተክሉ አያይዘውም፣ የእንሰት ሰብል ድርቅን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፣ ይህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሀገር በቀል ሰብል ቀጣዩ የምግብ ዋስትና መፍትሔ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አሁን ላይ እንደ ዩኒቨርሲቲ በእንሰት ሰብል ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሳይንሳዊ መንገድ የእንሰት ሰብል ሚናን በማላቅ ጠቀሜታውን ለማሳደግ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በሲምፖዚየሙ የተደረጉ ውይይቶች በእንሰት አምራች አርሶ አደሮች ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ተግባራዊ መፍትሔዎችን እና ፖሊሲዎችን እንደሚያመነጩ ዶ/ር ተክሉ ገልጸዋል።

 የ FAO Achievement Award 2026 አሸናፊ እና ቁልፍ ንግግር አቅራቢ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በበኩላቸው፣ አፍሪካ እጅግ ግዙፍ መሬት እና የውኃ ሀብት ቢኖራትም ከ300 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች በቂ ምግብ እንደማያገኙ እና ከአህጉሪቱ ውጭ የምግብ እህሎችን ለማስመጣት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ65 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን በቁልፍ ንግግራቸው ጠቁመዋል። እንሰት አነስተኛ ግብዓት የሚጠይቅ፣ በትንሽ ቦታ ብዙ ምግብ መስጠት የሚችል እና ድርቅን በብቃት መቋቋም የሚችል በመሆኑ ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና ትልቅ መፍትሔ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ለቤተሰብ ፍጆታ ብቻ ይታወቅ የነበረው እንሰት አሁን ላይ በአርሶ አደሮች ዘንድ እንደ ጥሬ ገንዘብ ማግኛ ሰብል (Cash Crop) እየተሸጠ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ፤ በሀገር ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም ራስን በምግብ ለመቻል እንደ እንሰት ባሉ ሀገር በቀል ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በመድረኩ ላይ የእንሰት ምርምር ታሪካዊ አመጣጥና የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር ገዛኸኝ ጋሮ፤ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንሰት ምርምር መነሻ የነበረው  Christensen Fund ድጋፍ ልዩ ልዩ የእንሰት ዝርያዎችን ለመጠበቅና ለማራባት የተመሰረተው የእንሰት ፓርክ (Enset Park) እንደነበር አስታውሰዋል። ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ በእንሰት ምርምር ዘርፍ ትልቅ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ግኝት ማስመዝገቡን የጠቀሱት ዶ/ር ገዛኸኝ፤ በተለይም የእንሰት ማቀነባበር እና ማብላላት (Fermentation) ሂደትን በዘመናዊ መንገድ በመቀየር የአርሶ አደሩን ህይወት በግልጽ የሚለውጡ ውጤቶች መመዝገባቸውን፣ ይህም በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና እንዳስገኘ ገልጸዋል። በተጨማሪም የእንሰት ምርትን በእጅጉ እየጎዳ የሚገኘውን የእንሰት አጠውልግ (Bacterial Wilt) በሽታ ለመከላከልና ከበሽታ  ነፃ የሆኑ የእንሰት ችግኞችን በብዛት ለማምረት የሚያስችል የቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪ (Enset Tissue Culture Laboratory) ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል።

የአላባስተር ኢንተርናሽናል መስራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሻነን ፈርናንዶ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በእንሰት ምርምር ሥራዎች ላይ ያሳየውን አስደናቂ ዕድገት በአካል በመገኘት መመልከታቸውን ገልጸዋል። ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በ FAO Achievement Award 2026 መሸለማቸው እጅግ ኩራት እንደሰጣቸው ገልጸው፤ ይህ ስኬት እንሰት ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና እና ለአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም (Climate Resilience) ምን ያህል ስትራቴጂካዊ እና ቁልፍ ሰብል መሆኑን የሚያሳይ ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ ነው ብለዋል። ድርጅታቸው ከ2022 ጀምሮ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቲሹ ከልቸር (Tissue Culture) ፕሮቶኮሎችን ማዘጋጀቱን፣ የተሳካ የመስክ ላይ ሙከራዎችን (Field Trials) ማካሄዱን፣ እንዲሁም አርሶ አደሮች እንሰትን በስፋት እንዲተክሉ ለመርዳት የሚያስችል የመጀመሪያው የሞባይል መተግበሪያ "Enset AI" በጋራ መጀመሩን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም እንሰት ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ጥናቶችና ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በሲምፖዚየሙ ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ለተሳታፊዎች፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ላቀረቡ ተመራማሪዎች እና ለአጋር ድርጅቶች (ስፖንሰሮች) የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል። በመጨረሻም የጉባኤው ታዳሚዎች በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የሚገኙትን የእንሰት ላቦራቶሪዎች፣ የኤግዚቢሽን ማዕከል (Showroom)፣ እና ሌሎች የምርምር ቦታዎችን በአካል ተዘዋውረው በመጎብኘት የሁለት ቀን ቆይታቸውን በስኬት አጠናቅቀዋል።

 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom

 ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

 ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት