የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የዶክትሬት ዲግሪ (PhD) ተመራቂ መምህራንን ለመቀበል እና በዶክትሬት ፕሮግራሞች መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ ለመወያየት ያለመ 5ኛውን "Doctoral Day" ዛሬ ሚያዝያ 28 ቀን 2018 . በዩኒቨርሲቲው አክብሯል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዕለቱ በተካሄደው መርሐ ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር /ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ / ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት፤ መድረኩ የዶክትሬት ትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን ለመገምገም እንዲሁም ለማኅበረሰቡና ለሀገር ጠቃሚ ምርምሮችንና ሕትመቶችን ያበረከቱ ነባርና አዲስ ምሩቃንን በማሰባሰቡ ልዩ ያደርገዋል። ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን በመቀመር የትምህርት አሰጣጡን ማሻሻል፣ የምርምርና ሕትመት ሥራዎችን በትብብር መሥራት እንዲሁም የሦስተኛ ዲግሪ ምሩቃንን ቁጥርና ማዕረግ በማሳደግ ዩኒቨርሲቲውን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ይስሃቅ ከቸሮ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ በምርምርና በፈጠራ ብቁ የሆኑ ምሁራንን በማፍራት ለሀገር እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው እየተገበረው ያለውን የለውጥ አቅጣጫ መነሻ በማድረግ በትምህርት፣ በምርምርና በተማሪዎች አገልግሎት ሦስት አዳዲስ የድህረ ምረቃ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች መከፈታቸውን ጠቁመዋል። በተጨማሪም በዶክትሬት ተማሪዎች ፈተና አሰጣጥና ማማከር፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ፖሊሲ፣ በክፍያ ሥርዓትና በመተዳደሪያ ደንቦች ዝግጅት ዙሪያ የተመዘገቡ ስኬቶችን እንዲሁም ከትምህርት ካላንደር፣ ከሥርዓተ ትምህርት ክለሳና ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ በቀጣይ መሻሻል የሚሹ ጉዳዮችን ለውይይት አቅርበዋል።

የድህረ ምረቃ ትምህርት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ / አለማየሁ ወርቁ እንደገለጹት፤ ምሩቃኑ የዩኒቨርሲቲውን ቁልፍ የሥራ አፈጻጸም አመልካቾች (KPI) ለማሳካት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሐምሌ 2025 ጀምሮ በሁለቱ ኢንስቲትዩቶችና በስድስቱ ኮሌጆች ውስጥ 38 አዲስ የዶክትሬት ዲግሪ ምሩቃን ማስመረቅ መቻሉን ተናግረዋል።

"Disaster Risk Management" የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪውን ያገኘው / አብርሃም ወርቁ በሰጠው አስተያየት፤ "በትምህርት ቆይታዬ የነበረኝ ብርቱ ጥረት እና የአማካሪዎቼ ያልተቋረጠ ድጋፍ ለዚህ የላቀ ማዕረግ እንድበቃ አግዞኛል" በማለት ምስጋናውን አቅርቧል።

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ አዲስ ተመራቂዎቹ ባቀረቧቸው በጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲሁም በቀጣይ መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ለምሩቃኑ አማካሪዎችም ላበረከቱት አስተዋፅኦ የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት