አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2017 ዓ/ም የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ጥር 15/2017 ዓ/ም ገምግሟል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተፈራረመውን የቁልፍ ተግባራት ስምምነት መሠረት በማድረግ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ የአፈጻጸም ጊዜያት ሁሉም ፈጻሚ አካላት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ዩኒቨርሲቲው የገባውን የሥራ ውል መሠረት በማድረግ በትኩረትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ይፍሩ ባቀረቡት ሪፖርት የትምህርት ጥራት፣  አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፣ የምርምርና ፈጠራ ሥራዎች ተደራሽነትና ፍትሐዊነት እንደሁም የሀገር በቀል ዕውቀትን ማጣጣምና ማሳደግ፣ የማኅበረሰብ ጉድኝትና የሳይንስ የባህል ግንባታ ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ማሳደግ፣ የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ፣ የሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማሳደግ፣ የትምህርት አመራርና አስተዳደር ማጠናከር፣ የትምህርት ተቋማትን አቅምና ብቃት ማጎልበት፣ የትምህርት መሠረተ ልማትና ፋሲሊቲ ማሳደግ  በሚሉ ስምንት ግቦች አንጻር የተከናውኑ ተግባራት አፈጻጸም እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮች፣ የመፍትሔ እርምጃዎችና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡

የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ረገድ እስከ በግማሽ ዓመቱ የ11 ሥርዓተ ትምህርቶች ክለሳ፣ የተማሪዎችና መምህራን የትምህርት ደረጃ ስብጥር፣ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎን መጨመር እና የድኅረ ምረቃ ትምህርትን ማሳደግ መሠራቱ ተገልጿል፡፡ ለተቋራጮች እና ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የማማከር አገልግሎቶችን መስጠት ታቅዶ እስከ 2ኛ ሩብ ዓመትለ67 ተቋራጮች የማማከር አገልግሎት መሰጠቱ እንዲሁም ነፃ የሕግ ጥብቅና፣ የምክር አገልግሎትና የሰነድ ዝግጅት መከናወኑም ተጠቅሷል፡፡

የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ፣ ሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማሳደግን አስመልክቶ በስድስት ወራት ለ703 ተማሪዎች የሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን ከ4 ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ 1433 ተማሪዎች ለተግባር ትምህርት ሥልጠና መውጣታቸው እንዲሁም የመምህራን የትምህርት ዕድልና አካዳሚክ ማዕረግ እድገት ክንውንም በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው የራስ ገዝ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋማዊ አሠራሮችን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለማሸጋገር በግማሽ ዓመቱ የሴኔት መተዳደሪያ ደንብ የተከለሰ ሲሆን ነባሩን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በመገምገምና ተዛማጅ ማጣቃሻዎችን በመመርመር የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ ተካሂዶ ለግምገማ መቅረቡ ተመላክቷል፡፡

በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት