የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 5ኛው ‹‹ሀገረሰባዊ ዕውቀት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት›› ሀገራዊ ዓውደ ጥናት ግንቦት 26/2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በዓውደ ጥናቱ ‹‹የአሪ ብሔረሰብ ባህላዊ የተፈጥሮ ሀብት ዕውቀት፣ እሳቤዎችና ክዋኔዎች››፣ ‹‹ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ››፣ ‹‹ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በጋሞ ሕዝብ፡- የኦቾሎ ደሬ ተሞክሮ›› እና ‹‹ሀገር በቀል ዕውቀት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፡- የጋሞ እና ኮንሶ ጥብቅ ደኖች›› የሚሉ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ክዋኔና እሳቤዎች ለአካባቢ ጥበቃና ለግጭት አፈታት ያላቸውን ሚና የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ጥናታዊ ጽሑፎቹ በዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩትና በሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ት/ክፍል መምህራንና ተመራማሪዎች የተሠሩ ናቸው፡፡
በጽሑፎቹ እንደተመለከተው ሀገር በቀል ዕውቀት፣ እሳቤዎችና ክዋኔዎች የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም ግጭቶችን በመከላከልና በመፍታት ረገድ ለበርካታ ዘመናት አዎንታዊ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዘመናዊነትና ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ለውጦች፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በፌዴራልና በአካባቢ አስተዳደር በቂ ትኩረት አለማግኘትና ሌሎችም ምክንያቶች ለሀገር በቀል እሴቶቹ አደጋ የጋረጡ ሆነዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ በጥቆማቸው ከመንግሥት አካላት ተገቢው ትኩረትና ዕውቅና እንዲሰጠው፣ ማኅበረሰብ መር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲጠናከር እንዲሁም የምርምር፣ የካርታና ዶኪዩሜንቴሽን ሥራዎች እንዲሠሩ ሃሣብ አቅርበዋል፡፡
የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሕክምና፣ በግብርና፣ በግጭት አፈታት፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በሌሎችም በርካታ መስኮች የእምቅ ባህልና ዕውቀት ባለቤት መሆኗ ለማኅበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እንዲሁም ምርምሮች እንዲካሄዱ ድጋፍ በማድረግ ሀገር በቀል ዕውቀትና ክዋኔዎች ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ በትኩረት ይሠራል፡፡
ዓውደ ጥናቱ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የክልሉና የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች እንዲሁም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት ያቀዷቸውን ሥራዎች የሚያጠናክር መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አርባ ምንጭ እና አካባቢው በርካታ ባህላዊ እሴቶችን ያቀፈ በመሆኑ ለዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ሀገር በቀል ዕውቀት ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር ተጣምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገርና ለሀገር ልማት እንዲውል ለሀገር በቀል ዕውቀት ያለንን የተሳሳተ ግንዛቤ ማረም ብሎም በምርምር ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አህመድ ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን ከማካሄድ ባሻገር የሥነ-ጥበብ ዘርፍን ለማሳደግ አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ሀገራዊ የትርጉምና የተርጓሚነት ሙያ ጉባዔ ማዘጋጀቱን አስታውሰው መሰል መድረኮች ልምድና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም፣ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ሙያዊ አቅምን ለመገንባት ፋይዳ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በዓውደ ጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት