አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹በAMU-IUC›› ፕሮጀክት በንዑስ ፕሮጀክት 7 አማካኝነት በዩኒቨርሲቲው አባያ ካምፓስ ያሠራውን የሕፃናት ማቆያ ጥር 15/2017 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ማእከሉ ለሕፃናቱ ደኅንነት ምቹ ተደርገው በተዘጋጁ የመጫወቻ፣ የመመገቢያ፣ የመተኛ፣ የመጸዳጃና ሌሎች ክፍሎች ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት ያሉ 30 ሕፃናትን ተቀብሎ በፕሮጀክቱ ሥልጠና በወሰዱ ተንከባካቢዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የሕፃናት ማቆያ ማእከሉን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በተረጋጋ መንፈስ ሥራቸውን እንዲሠሩ፣ ሕፃናቱ ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ ብሎም ዩኒቨርሲቲው የሠራተኞቹን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ ውጤታማ እንዲሆን የሕፃናት ማቆያ ማእከሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ተ/ም/ፕሬዝደንትና የ AMU-IUC ፕሮጀክት የሀገር ውስጥ አስተባባሪ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው በኮሚዩኒቲ ት/ቤቶቹ ከዐጸደ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር በጥሩ ውጤት ለከፍተኛ ትምህርት ሲያበቃ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው እየከፈታቸው ያሉ ማቆያዎች ለሕፃናቱ ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ ሚና ያላቸው እና ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች ላይ የሚሠራውን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሕፃናት ልጆች ያላቸው የዩንቨርሲቲው መምህራንና እና የአስተዳደር ሠራተኞች ተረጋግተው ሥራቸውን በመሥራት ስኬታማ እንዲሆኑ እንዲሁም ለተቋሙ ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ማእከሉ በዕውቀት፣ በሰው ኃይልና በቁሰቁስና ተጠናክሮ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡
የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የሕፃናት ማቆያ ማእከላት መኖራቸው ሕፃናት እናቶቻቸው ሥራ ላይ በመዋላቸው ተገቢውን እንክብካቤ እንዳያጡ ከማስቻሉም በላይ ሴት ሠራተኞች ልጆቻቸውን በቅርበት እየተከታተሉ በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን በማስተባበር እውን እንዲሆን ለሠሩ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበው ለቀጣይ ሥራዎች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
AMU-IUC ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ፕሮጀክቱ በሚያቀርበው የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል የሴቶች ተሳትፎ ማነሱን ተከትሎ በተደረገ ጥናት ሴቶች ከሕፃናት እንክብካቤና የቤት ውስጥ ኃላፊነት ጋር ተያይዞ የሚገጥማቸው ችግር በትምህርትና ምርምር ተሳትፏቸው አናሳ እንዲሆን ማድረጉ ተለይቷል ብለዋል፡፡ በዚህም መነሻነት ለዩንቨርሲቲው ሴት መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ልጆች ማቆያ የሚሆን ዘመናዊ የሕፃናት ማቆያ ለመሥራት ፕሮጀክቱ ማቀዱን ጠቁመዋል፡፡ በንዑስ ፕሮጀክት 7 አማካኝነት የተሠራው የሕፃናት ማቆያ ለሴት መምህራንና ሠራተኞች እፎይታ የሚፈጥር እና የሴቶችን የትምህርትና ምርምር ተሳትፎ የሚያሳድግ ነው ያሉት ዶ/ር ፋሲል የሴቶችን አቅም ከማጎልበት አንጻር ለማእከሉ ቀጣይነትና ውጤታማ ሥራ በባለቤትነት ስሜት በከፍተኛ ትኩረት መሥራት እንዲሁም ይበልጥ ማሳደግና ማስፋፋት እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በAMU-IUC ፕሮጀክት የንዑስ ፕሮጀክት 7 መሪ ዶ/ር ገናዬ ጸጋዬ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ የማእከሉን ቀጣይ ሥራዎች አስመልክቶ የመተዳደሪያ ደንብ፣ ሕጋዊ ፈቃድ፣ የክፍያ ሁኔታ፣ የአገልግሎት ጥራትና ቀጣይነት፣ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ተሞክሮውን በሌሎች ካምፓሶች ማስፋፋት ላይ ገለጻ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በገለጻው እንደተመለከተው አባያ ካምፓስ ለማእከሉ ባመቻቸው ቦታ ላይ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ለሕፃናቱ ምቹ የሆኑ ክፍሎች የተዘጋጁ ሲሆን አስፈላጊው ቁሳቁስ በግዢና በድጋፍ ተሟልቷል፡፡ በቀጣይ ሥራውን ከሚረከበው አካል ጋር በመቀናጀት የማእከሉን መተዳደሪያ ደንብ ማጽደቅና ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘት ላይ የሚሠራ ሲሆን ሌሎች የዩኒቨርሲቲውንና የካምፓሱን አመራሮች እንዲሁም ወላጆችን የሚያሳትፉ ቀጣይነት ያላቸው ተግባራትም እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡
የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ካምፓሱ የሕፃናት ማቆያ ማእከል እንዲኖር በወላጆች በኩል ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበር አስታውሰው የበርካታ ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን ችግር የሚቀርፍ በመሆኑ ሥራው እውን እንዲሆን ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ እንደ ኮሌጅ ለማእከሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተገኙ ወላጆች በማእከሉ መከፈት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ሕፃናት ልጆቻቸው ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው ሲውሉ ሳይሳቀቁና ሃሳባቸው ሳይከፋፈል ሥራዎቻቸውን ለመሥራትና ውጤታማ ለመሆን እንደሚረዳቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ማእከሉ ከዚህም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ የዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን የእኛ የወላጆችም ኃላፊነት ጭምር በመሆኑ የተቻለንን ሁሉ በማድረግ ልንደግፈው ይገባልም ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ለሥራው ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ እንዲሁም ሕጻናቱን ለመንከባከብ በፕሮጀክቱ ሥልጠና ለወሰዱ የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት