አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች "Acces Scholarship" የተሰኘ የሥልጠና ፕሮግራም የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጥር 17/2017 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ትምህርት ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ማግኘትና መፍጠር እንደሆነ ተናግረው የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ተማሪዎች ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል። በፕሮግራሙ ተማሪዎች ከቋንቋ ባሻገር የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የሚያውቁበት እንደሆነም ም/ፕሬዝደንቱ አክለዋል። ለፕሮግራሙ የተመረጣችሁ ተማሪዎች በውድድር የተለያችሁ አንደመሆናችሁ ለተሻለ ውጤት መትጋት አለባችሁ ያሉት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ወላጆችም በየጊዜው አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንድታደርጉ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአሜሪካ ኤምባሲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሪጂናል ጽ/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌና ሮዳስ (Dr. Gena Rhoades) የ"Access Scholarship" ፕሮግራም አሜሪካ በዓለም ላይ ከምትመራቸው ፕሮግራሞች መካከል ትልቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በሞሮኮ ይፋ ሆኖ የተጀመረው ፕሮግራሙ በእስከአሁን ቆይታው ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ወጣቶችን በ90 ሀገራት አሠልጥኖ አስመርቋል ብለዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ"Access Scholarship ዳይሬክተር ዶ/ር አባተ አንጁሎ በበኩላቸው "Access" ፕሮግራም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክሂሎትን ማሳደግ ላይ ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመንን በማጎልበት፣ በማኅበረሰብ ውስጥ ባለራእይ መሪዎችን ለማፍራት የሚሠራ ነው ብለዋል፡፡ ኘሮግራሙ አራት መሠረታዊ ዓላማዎች ያሉት መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አባተ ዓለም አቀፋዊነት፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብን መታጠቅ፣ የአሜሪካን እሴቶችና ባህልን ማወቅና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክሂሎትን ማሳደግ ናቸው ብለዋል፡፡ የ''Access " ፕሮግራም የውጭ ትምህርት ዕድል የሚገኝበት ብቻ ሳይሆን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተማሪዎች የፈጠራ፣ የሕይወት ክሂሎትና ሌሎች አዳዲስ አመለካከቶችን የሚያሳድጉበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶ/ር አዳነች ዘመዴ ሥልጠናው ለሁለት ዓመት የሚቆይ መሆኑን እና በአርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች በውድድር የተመረጡ 36 ተማሪዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።
በዕለቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪና የ"Access Scholarship" ፕሮግራሞ የቀድሞ ሠልጣኝ ህብስት አየሁ ተሞክሮዋን ለተማሪዎች ያካፈለች ሲሆን ፕሮግራሙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክሂሎትን ከማደበር ባሻገር ሌሎች በርካታ ለሕይወት አጋዥ የሆኑ ዕውቀትና ክሂሎቶችን ያገኘችበት እንደነበር አውስታለች።
ከጫሞ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ማሪቱ ወልዴ በ"Access Scholarship" ፕሮግራም የመሳተፍ ዕድል በማግኘቷ መደሰቷን ገልጻ ዕድሉን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዋን ለማሳደግ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላትን ማኅበራዊ መስተጋብር ለማጠናከር እንዲሁም የስኮላርሺፕ ዕድል በማገኘት የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደምትጠቀምበት ተናግራለች፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት