በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ "International AIDS Society (IAS)" ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በተመተባባር ዕድሜያቸው ከ10-19 ዓመት የሆኑ አፍላ ወጣቶች ዲጂታል ጤና አገልግሎትን በመጠቀም የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት አወሳሰድን ማሻሻል ላይ ያተኮረ የትብብር ምርምር ፕሮጀክት ጥቅምት 1/2018 ዓ/ም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምር ፕሮጀክቱ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅብረሰብ ጤና ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አባይነህ ቱንጄ የሦስተኛ ዲግሪ የጥናት ውጤታቸውን መሠረት አድረገው በዓለም አቀፍ ደረጃ በመወዳደር ከ"International AIDS Society (IAS)" ባገኙት 140 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ግራንት  ተግባራዊ የሚሆን አዲስ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ የሁለት ዓመት ቆይታ ያለው ሲሆን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ኮንሶና ደቡብ ኣሞ ዞኖች በሚገኙ  የኤች. አይ.ቪ ሕክምና በሚሰጡ 12 የጤና ተቋማት ተግባራዊ የሚሆን ነው።

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ የትብብር ምርምር ፕሮጀክቱ እንደ ዩኒቨርሲቲ መሰል የትብብር ፕሮጀክቶች በእጅጉ በሚበረታቱበት ወቅት ላይ የተገኘ መሆኑንና ሌሎች የኮሌጁ ተመራማሪዎችን በማነሳሳት ረገድም ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አባይነህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገ ውድድር ግራንቱን ካሸነፉ ሁለት ተመራማሪዎች መካከል አንዱ መሆናቸው እንደ ተቋም የሚያኮራን ነውም ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአፍላ ወጣቶች የፀረ ኤች.አይ.ቪ ሕክምና ሥራ ተገቢ የመድኃኒት አወሳሰድ ለማምጣት የሚረዳ ከወጣቶቹ ባሕርይ ጋር የሚሔድ አሠራር ይዞ የመጣ መሆኑንም ዶ/ር ደስታ ተናግረዋል። በቀጣይም በምርምሩ በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፀረ ኤች. አይ. ቪ ሕክምናና ተገቢ  የመድኃኒት አወሳሰድ አንጻር ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ አሠራሮችን ይዞ ሊመጣ የሚችል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክት ነው ሲሉም ዶ/ር ደስታ አውስተዋል፡፡

የምርምር ፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር አባይነህ ቱንጄ እንደገለጹት ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ዕድሚያቸው ከ10-19 ያሉ አፍላ ወጣቶች መድኃኒት መውሰድን በመርሳት፣ በጨዋታ በመዘናጋት፣ ሊደርስባቸው የሚችል መገለልን በመፍራት እና በሌሎች ምክንያቶች የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒትና ሕክምናን በአግባቡ አይወስዱም፡፡ መድኃኒቱን በአግባቡ አለመውሰድ  መድኃኒቱ ከሰውነት ጋር እንዲላመድ እንደሚያደርግ እንዲሁም በሰውነት ውስጥ የቫይረሱን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር የቫይረሱን በቀላሉ ወደ ሌሎች ሰዎች የመተላለፍ ዕድል ከፍ እንደሚያደርግ ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሁኔታ ሕሙማኑን ለከፍተኛ የጤና መታወክና በሂደት ለሞት ጭምር ሊዳርግ ይችላልም ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለዚህ ችግር መፍትሔ ለማበጀት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት አወሳሰድ ሁኔታን ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ ጥናት ማድረጋቸውን የገለጹት ዶ/ር አባይነህ በጥናታቸው የሞባይል ስልክን በመጠቀም ታካሚዎች መድኃኒታቸውን በሰዓቱ እንዲወስዱ ለማስታወስ አጭር የጽሑፍ መልእክት መላኪያ ሥርዓት በመንደፍ ተግባራዊ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። በዚህ ዘዴ የታካሚዎች መድኃኒት አወሳሰድ 34 በመቶ ያደገ መሆኑን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ተመራማሪው በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡

አዲስ የተጀመረው ፕሮጀክት ከዚህ በፊት በተደረገው ምርምር የመጣውን ውጤት ማስቀጠል ላይ ትኩርቱን አድርጎ የሚሠራ ሲሆን ለታካሚዎቹ እንደየ አወሳሰዳቸው ከሚላከው የማስታወሻ አጭር የጽሑፍ መልእክት በተጨማሪ መድኃኒት የሚወስዱበትን ሰዓት ከሌሌላ ነገር ጋር አገናኝተው እንዲላመዱት በማድረግ የመድኃኒት አወሳሳዳቸውን ይበልጥ ለማሻሻልና ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ ይሠራል ብለዋል። በጥናቱ 400 የሚሆኑ አፍላ ወጣቶች ይሳተፋሉ ያሉት ዶ/ር አባይነህ የመድኃኒት አወሳሰዳቸው /Adherence/ 95 ከመቶ በላይ የሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። በፕሮጀክቱ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ሁለት የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ጥናታቸውን እንዲሠሩ እንደሚደረግም ዋና ተመሪማሪው ገልጸዋል።

የምርምር ፕሮጀክቱ አማካሪ ዶ/ር ደጉ ጀረኔ በበኩላቸው የምርምር ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በተሠራው ምርምር የታየውን ውጤት ይበልጥ ለማዝለቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል። ለታዳጊ ወጣቶችም መድኃኒት በአግባቡ መውሰዳቸው በሰውነታቸው የሚኖረውን የቫይረስ ጫና በመቀነስ የተሻለና ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ ይረዳል ብለዋል። በምርምር ፕሮጀክቱ የሚሠሩ ሥራዎች በማኅበረሰብ ደረጃ የቫይረሱን ሥርጭት የመቀነስ ፋይዳ ይኖራቸዋል ያሉት ዶ/ር ደጉ በጥናቱ የሚገኘው ውጤትም ወደፊት በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያሉ አሠራሮችን በማሻሻል ረገድ እንደ ግብአት ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆኑንም ጠቅስዋል።

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርይሁን ዘርዶ የዕለቱ መርሃ ግብር ለምርምር ሥራው ውጤታማነት የሚሆኑ ግብአቶች የተገኙበት መሆኑን ተናግረዋል። ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድጋፍ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት ዶ/ር ዘርይሁን ለምርምር ሥራው ውጤታማነት እንደ ኮሌጅ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች የመድኃኒት ሰዓት መርሳት በፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት አወሳሰድ ላይ የሚስተዋል ዋነኛው ችግር በመሆኑ ከዚህ ቀደም በተደረገው ጥናት በየዕለቱ የማስታወሻ መልእክት በመላክ የተሠራው ሥራና የተገኘው ውጤት እንዲሁም ይህንን ሥራ ይበልጥ ለማጠናከር የተጀመረው አዲስ ፕሮጀክት የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለምርምር ሥራው መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል::

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት