የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት እና የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ለውኃ ቴክኖሎጂ እና ለቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የፕሮግራም ዕውቅና /Program Accreditation/ ሥራ ኮሚቴ አባላት ሀገር አቀፍ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የፕሮግራም ዕውቅና አሰጣጥ ላይ ባዘጋጀው መገምገሚያ መስፈርት ዙሪያ ታኅሣሥ 2/2017 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው አጀንዳ ሲሆን ይህን ለማሳካት የፕሮግራም ዕውቅና (Accreditation) አይነተኛ ሚና አለው፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት፣ ጥራት ያለው የትምህርት ግብአት፣ የሰው ኃይል፣ ቤተ ሙከራ፣ የኮምፕዩተር ማዕከል እና ብቃት ያለው የአስተዳደር ሥርዓት መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ በ2017 ዓ/ም ለ11 ፕሮግራሞች ዕውቅና ለማሰጠት ዕቅድ የተዘጋጀ ስለሆነ ለሥራው የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዶ/ር ሙሉነህ ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለሚዘጋጀው የፕሮግራም ዕውቅና አዘገጃጀት ሂደት፣ መስፈትና ይዘቱን አስመልክቶ ለኮሚቴው ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በ2017 ዕቅድ መሠረት በየፋከልቲው የሚገኙ ፕሮግራሞች በሀገር አቀፍ ደረጃ ተገምግመው ዕውቅና እንዲያገኙ ማስቻል የሥልጠናው ዋነኛ ዓላማ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት እየሄደ በመሆኑ ተወዳዳሪ፣ ብቁና ጥራታቸውን የጠበቁ ፕሮግራሞችን ለተማሪዎች ማዘጋጀት ተመራጭ ስለሚያደርገው አስቀድሞ የትምህርት ፕሮግራሞች ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ በበኩላቸው ትምህርት ሚኒስቴር በ2017 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የፕሮግራም ዕውቅና መስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም 11 የትምህርት ፕሮግራሞች  ዕውቅና እንዲያገኙ ለመሥራት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ተፈራርሟል ብለዋል፡፡ ሥራው ተቋማችን የሚገመገምበትና በቂ ትኩረትና ኃላፊነትን የሚሻ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በውኃ ቴክኖሎጂ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ለአራት ፕሮግራሞች ዕውቅና ለማሰጠት በመታሰቡ ሥርዓተ ትምህርቱን በአግባቡ ማየትና መረጃን መሠረት በማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተቋማዊ ጥራት አስተባባሪ ዶ/ር ሕይወት ጸጋዬ እንደ ዩኒቨርሲቲ በ2017 ዓ/ም በልዩ ትኩረት የፕሮግራም ዕውቅና ሥራ ለመሥራት በመታቀዱ ሥራውን በጥራት ማከናወን እንዲቻል የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት በአሠራሩ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሥልጠናው መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት