በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (AWTi) አዘጋጅነት “የአፍሪካን ውሃዎች በአህጉራዊ አንድነት መንፈስ ማገናኘት” (Harnessing Africa’s Waters in the Spirit of Continental Solidarity) በሚል መሪ ቃል ላለፉት ሁለት ቀናት በዩኒቨርሲቲው ሲካሄድ የነበረው 24ኛው ዓለም አቀፍ የዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት ሲምፖዚየም በስኬት ተጠናቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሚካኤል መሃሪ ባደረጉት ንግግር ይህ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ሳይንሳዊ ምርምርን ከፖሊሲ ቀራጮችና የዘርፉ ፈፃሚዎች ጋር የሚያስተሳስር ትልቅ አገራዊና አህጉራዊ ድልድይ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ በውሃ፣ በኃይልና በተፈጥሮ ሀብቶች እጅግ የበለጸገ ቢሆንም እየተፋጠነ የመጣው የአየር ንብረት መለዋወጥ፣ ያልተመጣጠነ የከተሞች መስፋፋት እና ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በዘርፉ ላይ ከባድ ጫና እና መዋቅራዊ ፈተናዎችን እየደቀኑ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል።
ዶክተር ሚካኤል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እነዚህን ተደራራቢ ፈተናዎች ለመቋቋም የተከተላቸውን ዋና ዋና ስልቶች ያብራሩ ሲሆን፣ በተለይም የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መርሆዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ የአቅርቦት ትኩረትን ከማስፋፋት ባለፈ የውሃ መሠረተ ልማቶችን ከታዳሽ ኃይል፣ በተለይም ከፀሐይና ከነፋስ ኃይል ጋር በማቀናጀት ዘላቂነት ያለው አሠራር እየዘረጋ መሆኑን በስፋት አብራርተዋል።
በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የሃይድሮሎጂ መረጃዎችን በማምረት ረገድ እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የምርምር ተቋማት ያላቸውን ሚና ያደነቁት አማካሪው ተቋማቱ አዳዲስ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን እና የዲጂታል ሞዴሊንግ ስራዎችን በማቅረብ የመንግስትን የረጅም ጊዜ የልማት ውሳኔዎች እንዲደግፉ እና በቀጣናው የሚታዩትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ኢንጂነር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው ይህንን ታላቅ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ላለፉት 24 ዓመታት ያለመቋረጥ ማስተናገድ መቻሉ ተቋሙ በውሃ ሳይንስና ምህንድስና ዘርፍ የገነባውን ጠንካራ አካዳሚካዊ ልህቀትና፣ የምርምር አቅምና የፈጠራ ባህል በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለውሃ፣ ለሃይድሮሎጂ እና ለአየር ንብረት ምርምሮች እጅግ ምቹና ተመራጭ የተፈጥሮ ላብራቶሪ በሆነ ስትራቴጂካዊ መልክዓ ምድር ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ፣ ተቋሙ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ወደ ተግባራዊ የፖሊሲ መፍትሄዎች በመቀየር ረገድ በአገር አቀፍና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ለመሆን እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው መዋቅራዊ የሆኑ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድና በመላው አህጉሪቱ እያጋጠሙ ያሉትን እንደ የውሃ ዋስትና እጥረት፣ የድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች ውስብስብነት፣ የአየር ንብረት መለዋወጥ እና የብዝሃ ሕይወት መመናመን ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዩኒቨርሲቲዎች ከባህላዊው የአሠራር ዘይቤ መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዓለም አቀፍ የልህቀት ማዕከላት፣ ከፖሊሲ አውጭዎች እና ከግል ዘርፉ (Private Sector) ጋር ያላቸውን ስልታዊና ተግባራዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ዩኒቨርሲቲው ይህንን አህጉራዊ ዓላማ ለማሳካት የምርምር መሠረተ ልማቶችን እንደሚያዘምን፣ የወደፊቱን የሰው ኃይልና ወጣት ተመራማሪዎችን በአዲስ እይታ እንደሚያበቃ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በትኩረት እንደሚያከናውን አረጋግጠዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ሲምፖዚየሙ የዩኒቨርሲቲውን የምርምርና የትብብር ስትራቴጂካዊ ግቦች ለማሳካት ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ አብራርተዋል።
ምክትል ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው በሲምፖዚየሙ ላይ የሚቀርቡት ሳይንሳዊ ጥናቶች በላቦራቶሪና በአካዳሚክ መጽሔቶች ላይ ብቻ ታጥረው መቅረት እንደሌለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ተቋሙ ዓለም አቀፍ ትብብሮችን በማጠናከርና የምርምር አቅምን በማሳደግ ረገድ ያሳየውን ዕድገት ያብራሩት ዶክተር ተክሉ፣ እነዚህን የምርምር ግኝቶች በቀጥታ ወደ ማህበረሰቡ በመውሰድና ከተግባራዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር በማቀናጀት በአካባቢው የሚገኙትን የውሃ ተፋሰሶች ለመጠበቅና የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የወደፊት የምርምር አቅጣጫዎችም በማህበረሰብ ተኮር መፍትሄዎች ላይ እንደሚያተኩሩ አብራርተዋል።
በሲምፖዚየሙ ላይ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥና ሜትሮሎጂ ፖሊሲ ኦፊሰር ወይዘሪት ፓሜላ ዊሊያም ሌቪራ ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር፤ የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ 2026ን የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እና አስተማማኝ የሳኒቴሽን ስርዓትን ማረጋገጫ ዓመት አድርጎ መሰየሙን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ አህጉር ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ንጹሕና ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኝ የጠቀሱት ኦፊሰሯ፣ ይህንን መዋቅራዊ ችግር ለመፍታት አህጉራዊ አንድነትና የተቀናጀ ስራ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። ውሃ በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በምግብ ዋስትና እና በሕዝብ ጤና ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያለው ዋነኛ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ግብዓት በመሆኑ፣ የአፍሪካን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ የአህጉሪቱ የውሃ ምርታማነት (Water Productivity) በከፍተኛ ደረጃ ማደግ እንዳለበት በጥብቅ አሳስበዋል።
ወይዘሪት ፓሜላ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደው የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ለአፍሪካ አህጉር የአየር ንብረት ፋይናንስን በማሰባሰብ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የመላመድ (Adaptation) አቅምን በመገንባት ረገድ ታላቅ የፖሊሲ መድረክ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። በመሆኑም እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ሳይንሳዊ ግኝቶቻቸውን እና የሃይድሮ-ዲፕሎማሲ እውቀቶቻቸውን በቀጥታ ወደ ተግባር በመቀየር፣ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ስኬታማ እንዲሆን ማዕከላዊና መሪ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (AWTi) ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምሩ ተሰማ እንደገለጹት ለዘንድሮው ሲምፖዚየም ከበርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተመራማሪዎች ከተላኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የምርምር ስራዎች መካከል በጥብቅ ሳይንሳዊ መስፈርት የተመረጡ 18 የጥናትና ምርምር ወረቀቶች ለቃል ማብራሪያ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ሲምፖዚያሙ በዘርፉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስቻሉ ስድስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ አተኩሮ የተካሄደ ሲሆን፣ ሃይድሮሎጂና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር (Hydrology and Integrated Water Resources Management)፣ ታዳሽ ኃይል (Renewable Energy)፣ በመስኖና ፍሳሽ ማስወገጃ (Irrigation and Drainage)፣ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን (Water Supply and Sanitation) እንዲሁም አየር ንብረት ለውጥ፣ ተለዋዋጭነትና ተፅዕኖዎች (Climate Change, Variability and Impacts) መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሲምፖዚየሙ ማጠቃለያ ላይ ለቁልፍ ንግግር አቅራቢዎች (Keynote Speakers)፣ በጥናትና ምርምር ወረቀት አቅራቢዎች (Paper Presenters) እንዲሁም ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አጋር አካላትና ተባባሪዎች (Collaborators) በሙሉ ላበረከቱት ሳይንሳዊና ስትራቴጂካዊ አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠት የተዘጋጁ የክብር የምስክር ወረቀቶች (Certificates) በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እጅ ተበርክተዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት


