የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅብረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት በምርምር ትብብር ፕሮጀክቶች ችግሮችና ዕድሎች ዙሪያ ሐምሌ 13/2016 ምክክር አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የትብብር ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሃሳብ አሁን ላይ ለምርምር ተብሎ ቀጥታ ከመንግሥት የሚገኘው በጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተመራማሪዎች ከተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሚሠሩ የትብብር ምርምር ሥራዎች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው በጽሑፋቸው ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የትብብር  ምርምር  ፕሮጀክቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ዶ/ር ቶማስ ቁጥሩ ካለን አቅምና ስፋት አንጻር ግን አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ የምርምር ማዕከላትን ለመክፈት እየሠራ መሆኑ እንዲሁም ተቋሙ በተለያዩ ዓለማት ከሚገኙ ተባባሪዎች ጋር አብሮ የመሥራት ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑ በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውንም ዶ/ር ቶማስ አክለዋል፡፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ምግብ፣ ውኃ፣ ኢነርጂ፣ ጤና፣ አኗኗር፣ ዘላቂ ልማት ወዘተ. ለትብብር ፕሮጀክቶች ለውድድር በስፋት የሚወጡ የውድድር ዘርፎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ለዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች በትብብር ፕሮጀክቶች ግራንት ፕሮፖዛል አፃፃፍና አስተዳደር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት፣ በኮሌጅና በትምህርት ክፍል/ፋከልቲ ደረጃ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል የሚያዘጋጅ ቡድን ማዋቀር፣ የመንግሥትን ፍላጎትና የሕዝብን ችግር መሠረት ያደረጉ ዘርፎች ላይ የግራንት ፕሮፖዛሎችን ማዘጋጀት፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ማጠናከር፣ መረጃዎችን በዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ አደራጅቶ ማስቀመጥ፣ በፋይናንስ አሠራር ላይ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ፣ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ቀጠናዊ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአካዳሚክና ምርምር ተኮር ማኅበራት አባል እንዲሆን ማድረግ፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የትብብር ፕሮጀክቶች ግራንት ፕሮፖዛሎችን የሚገመግም አማካሪ ቦርድ ማቋቋም እንዲሁም በኅትመት፣ ብሮድካስት፣ ማኅበራዊና ሌሎች የሚዲያ አማራጮች ስትራቴጂካዊ ተግባቦት በወቅቱ መሥራት በምክክር መድረኩ በተሳታፊዎች ከተነሱ ሃሳቦች መካከል ጥቅቶቹ ናቸው፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ገንቢ ሃሳቦች ምስጋናቸውን አቅርበው እንደ ዘርፍም ሆነ እንደ ዩኒቨርሲቲ በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ከተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ተቋማት ጋር በትብብር የመሥራት ባህል እያዳበረ መምጣቱን አውስተው በቅርቡም ሩሲያ ሀገር ከሚገኝ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መሥራት ጀምሯል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ ተባባሪ አካላትን የሚስቡ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን ‹‹Good Financial Grant Practices›› የተሰኘ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘትም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት