ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የጤናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ሰኔ 6/2017 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የሥራ እንቅስቃሴና ግብዓቶች ጎብኝተዋል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ባስተላለፉት የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ዩኒቨርሲቲው የአርባ ምንጭን ተፈጥሯዊ ገጽታ እና ከዞኑ ተራራማ አካባቢዎች የሚፈሱ ውኃማ አካላትን መነሻ በማድረግ በቂ የጥናትና ምርምር ሥራ ከመሥራት ባለፈ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በርካታ የተማሩ ዜጎችን በማፍራት ሀገራዊ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት፣ የመማር ማስተማርና ምርምር ሥራዎችን በሙሉ አቅሙ መስጠት እንዲችል በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ዶ/ር ተክሉ አክለዋል። 

የዩኒቨርሲቲው ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ጉብኝቱ በጤና ተቋማት መካከል የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ በማካሄድ ለማኀበረሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በትብብር መሥራት በሚቻልበት ዙሪያ ምክክር ለማካሄድ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹ግዙፉን ሆስፒታል ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ የማስገባት ሂደት ቀላል አይደለ›› ያሉት  ዶ/ር ደስታ  በተመላላሽ ሕክምና፣ የላቦራቶሪ እንዲሁም የሲቲ ስካን እና መሰል አገልግሎት በመስጠት ማኀበረሰቡን ከአላስፈላጊ ወጭና እንግልት መታደግ መቻሉን እንዲሁም የሰው ኃይል ከማሟላት አንጻር ሰፊ ሥራ መሠራቱን አስገንዝበዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የተኝቶ ሕክምና አገልግሎት ለማስጀመር እና በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና በአርባ ምንጭ ጠቅላላ ሆስፒታል ሲሰጡ የቆዩ ተግባር ተኮር የትምህርትና መሰል ሥልጠናዎች በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንም አውስተዋል። 

በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ማሻሻያ ሥራ አስሰፈጻሚ አቶ አሰግድ ሳሙኤል ጉብኝቱ የሆስፒታሉን የሥራ እንቅስቃሴ መገምገምና ልምድ መቅሰምን ዓላማ የደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ እና የበሽታ ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የዩኒቨርሲው ሆስፒታል የቦርድ አባል አቶ ዮሴፍ ሶንቆ ሆስፒታሉን በግብዓትና በሰው ኃይል ይበልጥ ለማደራጀት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክተር አቶ አምሳሉ ተስፋዬ በበኩላቸው ጉብኝቱ በሕክምና ተቋማት የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መለየት፣ ክፍተቶችን መሙላት እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ማድረግን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ጉብኝቱ 11ኛው ሀገር አቀፍ የጤናው ዘርፍ የሰው ሀብት አስተዳደር የምክክር ፎረም በአርባ ምንጭ መካሄዱን አስመልክቶ መዘጋጀቱንም አክለዋል።

በጉብኝቱ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሰው ሀብት አስተዳደሮች፣ የትምህርት ተቋማት አመራር አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት