በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት "Integrated Sustainable Land Management Strategies for a Sustainable Future" በሚል ርእስ ታኅሣሥ 24/2017 ዓ/ም በዘላቂ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ላይ ያተኮረ የሥልጠና ወርክሾፕ አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በመርሃ ግብሩ ላይ ከሦስት ዞኖችና ከዐሥራ ሁለት ወረዳዎች የተወጣጡ የግብርና ልማት፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የግብርና ስጋት አስተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ30 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ምርምሮች ወደ ማኅበረሰብ የሚወርዱና የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲሁም ለሀገር ፋይዳ ያላቸው እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው አሠራሮችን ዘርግቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በጫሞና አባያ ሐይቆች እና ተፋሰስ ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው ሲደረጉ የነበሩ የምርምር ሥራዎች ከዚህ አንጻር ተጠቃሾች ናቸው ያሉት ዶ/ር ፋሲል ከችግሩ አንገብጋቢነት አንጻር የምርምር ውጤቶችን በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማሳወቅና በማስረጽ በሚፈለገው ልክ ለውጥ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ውጤታማ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የማኅበረሰቡና የባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ፋሲል ከዚህ አንጻር በፕሮጀክቱ የተዘጋጀው የሥልጠና ወርክሾፕ ትልቅ ጥቅም ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት የንዑስ ፕሮጀክት ሁለት አስተባባሪ ዶ/ር አሸናፊ ዱጉማ ወርክሾፑ በዋናነት በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ሥር ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ላይ በተከናወኑ ምርምሮች ላይ የተመሠረተ ምክክር ለማድረግና ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የመሬት መራቆትን ጠንቅቆ መረዳት፣ ዘላቂ የመሬት አስተዳደር (SLM) አሠራርን መመርመርና ማጎልበት የሥልጠናው ዋነኛ ትኩረት መሆኑንም አስተባባሪው አክለዋል፡፡ 

በመርሃ ግብሩ በመሬት መራቆት እና በዘላቂ የመሬት አያያዝ አሠራርና ፖሊሲ ላይ ያተኮሩ ሁለት ሰነዶች በዕጩ ዶ/ር ጥላሁን ሀብታሙ የቀረቡ ሲሆን በዚህም የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ያለውን ትስስር በአጽንኦት ለተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል፡፡ ዕጩ ዶ/ር ጥላሁን በዘርፉ ላይ ያሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ማዕቀፎችንና ስምምነቶችን በማንሳት ሥራው በምን አግባብ መመራት እንዳለበትም ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡

በቀረቡት ሰነዶች ላይ ተሳታፊዎች ሰፋ ያለ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን ዘላቂ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማንሳትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመጠቆም የበኩላቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ላይ ለሚሠራው ዘላቂ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ፕሮጀክት ስኬትም የሚጠበቅባቸውን አተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አረጋግጠዋል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት