አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤልጂየም ከሚገኙ 5 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር የሚሠራው "AMU-IUC" ፕሮጀክት የፕሮጀክቱን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ አሠራሮች፣ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ ፕሮጀክቱ ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የፈጠራቸውን መልካም አጋጣሚዎች እና ወደ መሬት የወረዱ የምርምር ሥራዎችን አስመልክቶ ለዩኒቨርሲቲው አዲስ ከፍተኛ አመራሮች ገለጻ አቅርቦ ውይይት አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ከቀረበው ገለጻ ፕሮጀክቱ ተማሪዎችን ከማስተማር ባሻገር ዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ኢ/ር አብደላ በዋናነት በፕሮጀክቱ በምርምር የተገኙ ውጤቶችና ዕውቀቶች ላይ በመመሥረት እየተሠሩ ያሉ የኢንተርቬንሽን ሥራዎች እንደ ዩኒቨርሲቲ የሚያኮሩ ናቸውም ብለዋል፡፡ 

በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ቤተ ሙከራዎችን ከማደራጀት እንዲሁም የICT መሠረተ ልማት አቅምን ከማሳደግና ከማዘመን አንጻር በትብብር ፕሮጀክቱ የተሠራው ሥራ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ራስ ገዝ ለመሆን እንደሚሠራ ተቋም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የተፈጠሩ አቅሞችን ሙሉ በሙሉ የመጠቀም ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ በቀጣይ ፕሮጀክቱ ለሚሠራቸው ማናቸውም ሥራዎች በዩኒቨርሲቲው በኩል የሚጠበቁ ድጋፎችን ለማድረግ እንደ ተቋም ቁርጠኝነት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ፕሮጀክቱ በተለይ በ2ኛው ምዕራፍ ከአካባቢ፣ ከአፈርና ውኃ፣ ከሐይቅ ጥበቃ ወዘተ አንጻር እየሠራቸው ያላቸው ምርምርን ወደ መሬት የማውረድና ማኅበረሰብን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራዎች በእጅጉ የሚደነቁና እንደ ዩኒቨርሲቲ ልምድ ሊወሰድባቸው የሚገቡ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት በተለይ የዩኒቨርሲቲውን ሦሰት ተልእኮዎች ከመደገፍ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኒቨርሲቲውን ገጽታና እይታ ከመጨመር አንጻር ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረው ዘርፉን እንደሚመራ ኃላፊ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገብረማርያም በበኩላቸው ከቀረበው ገለጻ ፕሮጀክቱ በእጅጉ የላቁ ተግባራትን እየሠራ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረው በተለይ የምርምር ውጤትን ወደ መሬት ከማውረድ አንጻር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ልምድን በማከፈል ተሞክሮውን ማስፋት ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ በፕሮጀክቱ የተገኙ እንደ ድሮን ያሉና በቤተ ሙከራ ውስጥ የተደራጁ ግብአቶችንና መሣሪያዎችን በስፋት መጠቀምና ለተለያዩ የምርምርና ልማት ሥራዎች ማዋል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ለሥራ ኃላፊዎቹ ባቀረቡት ገለጻ በ‹‹VLIR-UOS›› እና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መካከል እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ ትብብር የተጀመረ ሲሆን ትብብሩ በ‹‹Stripes›› ፕሮጀክት የተጀመረ መሆኑንና በዚህ ፕሮጀክት በታየው ውጤታማነት ዛሬ ላይ ዩኒቨርሲቲው ጎልቶ የሚታይበት የእንሰት ፕሮጀክት መምጣቱን አስታውሰዋል፡፡ በሁለቱ የትብብር ፕሮጀክቶች 4 የዩኒቨርሲቲው መምህራን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተማሩ ሲሆን በሁለቱ ፕሮጀክቶች በታየው አመርቂ ውጤት ምክንያት ለ10 ዓመታት የሚቆየው የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2017 ይፋ ሆኖ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እስከ አሁን ባለው ቆይታ በሁለት ዙሮች 33 የዩኒቨርሲቲው መምህራን ቤልጂየም በሚገኙ 5 ዩኒቨርሲቲዎች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የመማር እና የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት የሚያስችሉ ምርምሮችን የማከናወን ዕድል የሰጠ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 14ቱ ትምህርታቸውን አጠናቀው ዩኒቨርሲቲውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የትብብር ሥራው በዩኒቨርሲቲ አቅም ሊሠሩ የማይቻሉ በርካታ የምርምር ሥራዎችና ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማርና ምርምር አቅም ከመገንባት አንጻርም አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ ጣቢያዎችና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የምርምር ቤተ ሙከራዎች በዩኒቨርሲቲው መደራጀታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የዩኒቨርሲቲውን የICT መሠረተ ልማቶች የማጎልበት ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል በምርምር በተገኙ ውጤቶችና ዕውቀቶች ላይ በመመሥረት በተለይ በ2ኛው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ በርካታ ምርምርን ወደ መሬት የማውረድ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዕለቱ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በተገኙ አዳዲስ የምርምር ዕውቀቶች ላይ ተመሥርተው እየተሠሩ የሚገኙ ዘላቂ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች፣ የሐይቅ ረግረጋማ ሥፍራን መልሶ የማልማት፣ አዳዲስ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ፣ የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ አዘገጃጀት፣ ት/ቤቶችን በአይ ሲቲ መሠረተ ልማት የማደራጀት እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው የተብራራ ሲሆን በቀጣይም እነዚህን ተግባራት የማስቀጠልና የማጠናከር ዕቅድ መኖሩ ተጠቁሟል፡፡ በመርሃ ግብሩ መጨረሻ ላይ ላለፉት አራት አመታት የፕሮጀክቱ የሀገር ውስጥ አስተባባሪ ሆነው ሲሠሩ ለቆዩት የቀድሞው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ለፕሮጀክቱ ስኬት ለተጫወቱት ሚና ምስጋና የቀረበ ሲሆን የማስተባበር ኃላፊነታቸውንም ለዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በይፋ አስረክበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት