በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት፣ ከፌደራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ከኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው 10ኛው አገርአቀፍ የሕግ ተማሪዎች "ምስለ ችሎት" (Moot Court) ውድድር በደማቅ የፍጻሜ መርሃግብር ተጠናቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ከግንቦት 7-9 2018 ዓ.ም በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ከፍተኛ የፌደራል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሕግ ባለሙያዎችና ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወከሉ ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን ውድድሩ በአርባ ምንጭ፣ በሰላሌ እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች አሸናፊነት ተጠናቋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጅነር አብደላ ከማል በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ውድድሩ የተማሪዎችን የሕግ ዕውቀት፣ የክርክር ብቃት፣ የሙያ ሥነ-ምግባር እና የፍትሕ አስተሳሰብ በተግባር የሚንፀባረቅበት ከመሆኑ ባለፈ ለሀገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት መጠናከር ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት መሰል የትምህርት ጥራትን የሚያሻሽሉ መድረኮችን ከማዘጋጀት ባሻገር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ 24 ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም አቅመ ደካማ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ዓመታት ከ85 ሺህ በላይ ምሁራንን በማፍራት ለሀገር ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በታዳሽ ኃይል እንዲሁም በሁሉም ኮሌጆች በርካታ የምርምርና የማኅበረሰብ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የፌደራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ተልእኮ መነሻ በማድረግ ነጻ የሕግ አገልግሎት ማዕከላትን ከመደገፍና ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር ላለፉት 9 ዓመታት ሀገር አቀፍ የሕግ ተማሪዎች የምስለ ችሎት ውድድሮችን በማስተባበር በበላይነት ሲመራ መቆየቱን ተናግረዋል።
የፍትሕ ሰጭ አካላት የብቃት ማነስ ለፍትሕ ሥርዓቱ አለመሻሻል ምክንያት መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ደግፌ፣ የሕግ ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በሰዎች ሕይወት ላይ እንደሚፈርዱ ሊያውቁና ሙያቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ቀልጣፋ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል። በውድድሩ በአሸናፊነት ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች ከምረቃ በኋላ የቅድመ ሥራ ሥልጠና እና በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ላይ በቀጥታ ተቀጥረው እንዲሰሩ ኢንስቲትዩቱ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ቃል ገብተዋል።
የፌደራል ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት በርካታ ግጭቶችን ላሳለፈችው እና በሽግግር ፍትህ ሥርዓት ውስጥ ለምትገኘው ለዚች ሀገር በቂ የሕግ ዕውቀትና ግንዛቤን በማስጨበጥ የተሻለ ፍትሕ ተደራሽ እንዲሆን በተማሪዎች መካከል የሚካሄዱ የምስለ ችሎት ውድድሮች እጅጉኑ ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የሽግግር ፍትሕ እንዲሰፍን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ የሽግግር ፍትሕ ዋና ዓላማው እውነትን በማፈላለግ ዲሞክራሲና ዘላቂ ሰላም ማስፈን መሆኑንና ለዚህም እንደ ሩዋንዳ፣ ሴራልዮን እንዲሁም ኮሎምቢያ ያሉ ሀገራትን በምሳሌነት አንስተው፣ በውድድሩ በአንደኝነት ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች ከተመረቁ በኋላ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቀጥታ የመቀጠር ዕድል የሚያገኙ መሆናቸውን አብስረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ውድድሩ ከእውነተኛው የፍትሕ አሰጣጥ ሂደት ጋር የተጣመረና ሴት ተፎካካሪዎች ልቀው የታዩበት ዓላማውን ያሳካ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት በደቡብ ኢትዮጵያ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን እና ለፍትሕ አካላት የሚሰጡ ሥልጠናዎችን ጨምሮ ለፍትሕ ሥርዓቱ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል። በመጨረሻም መርሃ ግብሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን ጥረት ላደረጉት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት መምህራን፣ ለአዘጋጅ ኮሚቴው እንዲሁም ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሕግ ት/ቤቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ማኅበሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የሕግ ትምህርት ቤቶችን የትምህርት ጥራት ለማሻሻልና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ስኬት ማኅበሩ የሕግ አንቀጾችን በማርቀቅ፣ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ መድረኮችን በማዘጋጀትና ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን በማጋራት በርካታ አበረታች ሥራዎችን ማከናወኑን አብራርተዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ ዳኞች፣ ተማሪዎችና አሰልጣኝ መምህራን እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የዋንጫ፣ የሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ ውድድሩም የሕግ ማኅበረሰብ የተገናኙበትና የነገን የፍትሕ መሪዎች የታዩበት ደማቅ ታሪካዊ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት


