የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከስዊዘርላንድ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ (SDC) እና ከ ETH Zürich ጋር በመተባበር ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው የ RUNRES ፕሮጀክት አማካኝነት፣ በጋሞ ዞን ብርብር ከተማ አስፈላጊ ቆሻሻን ሳይንሳዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ወደ ኮምፖስት (ተፈጥሮ ማዳበሪያ) ምርት የሚቀይር የቴክኖሎጂ ርክክብ ስነ-ስርዓት ዛሬ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በብርብር ከተማ ተካሂዷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የ RUNRES ፕሮጀክት በስዊዘርላንድ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ በ4 የአፍሪካ ሀገራት (ኢትዮጵያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ) በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ላይ የሚሰራ የምርምርና ልማት ስራ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ኢንቨስት የተደረገበት፣ ሳይንስን፣ ፈጠራንና መሰረተ-ልማትን ያቀናጀ ግዙፍ ተግባር መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝደንቱ፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአርባ ምንጭ ከተማ የኮምፖስት የሚያምርት ማህበርን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በማቅረብ ከመደገፍ ባለፈ፣ የሙዝ ዱቄት የሚያመርት አዲስ ማህበረን አሰራር የሚያሻሻሉ ዘመናዊ ማምረቻ ማሽኖችን በመስጠት ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ምርት እንዲያመርት ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት 3 የቆሻሻ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን (Trucks) በማበርከት ለዘርፉ ስራ መዘመን ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው፤ እነዚህ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች የአምራቾቹን ስራ ከልማዳዊ የእጅ ስራ ወደ ዘመናዊ የምርት ሂደት ያሸጋገሩ፣ ጊዜና ጉልበትን የቆጠቡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ዶ/ር ተክሉ አክለውም በዕለቱ የተላለፈው ቴክኖሎጂ የዚሁ የአንደኛው ምዕራፍ ስራ ማስፋት (scaling up) መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ከፍተኛ የሙዝ ምርት አቅም ባለው ምዕራብ አባያ አካባቢ የሚታየውን ከፍተኛ የኮምፖስት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል አስረድተዋል። ይህ ቴክኖሎጂ ንፁህ ከተማን ከመፍጠር ባለፈ በአለም አቀፍ ገበያ ላይ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ኦርጋኒክ ግብርና ምርትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጠቀሜታ እንዳለውና ከሀገሪቱ ብሔራዊ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂና ፖሊሲዎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም መሆኑን አረጋግጠዋል።
የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ ተወካይና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማጌሶ ማሾሌ በበኩላቸው፤ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዞኑ በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በርካታ አርአያነት ያላቸውን ተግባራት ማከናወኑን ገልጸው፤ የግብርና ተረፈ ምርቶችን መልሶ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለውጥ እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል። ቆሻሻን ወደ ጥቅም ለመቀየር እየተደረገ የሚገኘው ጥረት ቀጣይነት እንዲኖረው ዞኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።
የብርብር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም አይካ በበኩላቸው በከተማዋ ቆሻሻን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማስወገድ የሚያስችል ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ዘዴና ቴክኖሎጂ ይፋ በመደረጉ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ለፕሮጀክቱ አጋሮች ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። ይህ ፕሮጀክት ከተማዋን ፅዱ፣ ሳቢና ምቹ ከማድረጉም በላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያገኙ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የስዊዘርላንድ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ ተወካይ ወ/ሮ ቪቪያን ኦሴሌ (Mrs. Vivien Osele) ባስተላለፉት መልዕክት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የኮምፖስት አምራች ማህበሩ ተመስርቶ ምርት ጀምሮ እና በአሁኑ ሰዓት ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጁ ሆኖ በመገኘቱ የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልጸዋል። የታቀደው እቅድ በተግባር ተተርጉሞ መሬት ላይ መውረዱን ማየት መቻሉ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህ ስኬት መገኘት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት በሙሉ አድናቆታቸውን አቅርበዋል። በቀጣይም በጋራ በመስራት በአካባቢውና በዞኑ የላቀ ለውጥ ለማምጣትና የኮምፖስት ምርቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ትብብር እንዲደረግ አሳስበዋል።
የ RUNRES ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ፈይሶ ስለ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ ዋና ተልዕኮ የአካባቢ ቆሻሻን ወደ ግብርና ግብዓት መቀየር (Circular Economy) እንደሆነ ገልጸዋል። በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የተፈጥሮ ንጥረ-ነገሮች ስርጭት (Nutrient Loop) በማስተካከል የከተማ ቀጣና የምግብ ስርዓትን ማጠናከር ዋነኛው ግብ መሆኑን አብራርተዋል። አቶ አባይነህ አክለውም ፕሮጀክቱ የአካባቢ ጥበቃን ከመጠበቅ ባሻገር ዘርፉ ለበርካቶች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
በዚህ ፕሮጀክት ድጋፍ የተደራጀው "የብርብር ኮምፖስት አምራች ማህበር" በየ25 እና 30 ቀናት ውስጥ 133.76 ቶን ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ በማቀነባበር 86.95 ቶን ጥራት ያለው ተፈጥሮአዊ ማዳበሪያ ማምረት እንደሚችልና ለ 26 ሰዎች ቀጥታ የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ በዕለቱ ተጠቁሟል።
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ፕሮጀክቱ ከተማን ከገጠር የሚያስተሳስር ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የተገኘውን የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅም ይበልጥ ለማስፋት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ /Spring of Wisdom
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት


