የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነባር እና አዲስ የተመደቡ ከፍተኛ አመራሮች የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት እና የትምህርት ሚኒስቴር አረካካቢ ልዑካን በተገኙበት ታኅሣሥ 1/2017 ዓ/ም ሽኝትና ትውውቅ አድርገዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር የተቋማዊ ለውጥ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ግዛው እንደገለጹት ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ውጤታማነት ለማሳደግ የሪፎርም አጀንዳዎችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን የዩኒቨርሲቲዎችን ዓለም አቀፋዊነት ባረጋገጠ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የአመራር መተካካት ከሪፎርም ሥራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው የአመራር ለውጥም የዚህ ሥራ አካል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ከበደ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላትም ሆነ ማኅበረሰብ አዲስ ለተመደቡት አመራሮች አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አቶ ከበደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን ሒደት ላይ መሆኑን አስታውሰው ራስ ገዝ ሲኮን ተቋማዊ አቅምና ገጽታ በመገንባት ተማሪ ወዶና መርጦ የሚመጣበት ተቋም መሆን ካልተቻለ እንደ ተቋም የመቀጠል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ችግሮች ሲገጥሙ በጋራና በአግባቡ እየፈቱ የተቋሙን ጥቅም በማስቀደም መሥራት የሕልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መምራት አስቸጋሪና ብርቱ ሥራ የሚጠይቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው የቀደሙት አመራሮች ላበረከቱት አስተዋጽኦ በሚኒስቴሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለአዳዲስ አመራሮች መልካም ምኞታቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ፕሬዝደንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) በመማር፣ በማስተማርና በአመራርነት በቆዩባቸው በርካታ ዓመታት የተለያዩ ሰዎች ድጋፍና እገዛ ያልተለያቸው በመሆኑ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በኃላፊነት ዘመናቸው የዩኒቨርሲቲውን ስትራቴጂክ ዕቅድና ሀገራዊ አቅጣጫዎች በመከተል የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሲሠሩ መቆየታቸውን የጠቆሙት ፕሬዝደንቱ አዲስ የመጣው አመራር ትልቅ የለውጥ ሥራ የሚጠብቀው እንደመሆኑ ከካውንስሉና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በቅርበትና በመልካም መግባባት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ዳምጠው ከዚህ ቀደም በየጊዜው በተደረጉ ምልከታዎች ተለይተው የተቀመጡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ይህም በቀጣይ ጊዜያት ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡ ዶ/ር ዳምጠው ተቋሙን የሚያዳክሙና ገጽታውን የሚያበላሹ አሉታዊ መልእክቶችን ከማሰራጨት ይልቅ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር ተቀራርቦ መሥራት፣ ችግሮችን መፍታትና ደካማ ጎኖች እንዲሻሻሉ ጥቆማ መስጠት ይገባልም ብለዋል፡፡
አዲሱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ኢ/ር አብደላ ከማል (ዶ/ር) በ1993 ዓ/ም የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ ሆነው ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ረዥም ጊዜ ማሳለፋቸውን አስታውሰው የምወደውን ተቋምና ማኅበረሰብ ለማገልገል ኃላፊነት ስለተሰጠኝ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ የሙያና የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ በርካታ ምሁራንን ያፈራ ተቋምን ማገልገል ክብርና ትልቅ ዕድል ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ከቀድሞ አመራሮችና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ይህንን ትልቅ ኃላፊነት በጋራ ለመወጣት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝ ተቋምነት ለመሻገር ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለሙያዎችን መቅጠርና ማብቃት የሚጠበቅበት ሲሆን ለዚህም የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ መፍጠርና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም በመስክ ልየታው መሠረት እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲነቱ ማኅበረሰቡን በተግባር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርምሮችን ማከናወን እንዲሁም ነባሩ አመራር በትጋት ሠርቶ ያስረከበንን የመማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሺያላይዝድ ሆስፒታል በሙሉ አቅሙ እንዲያገለግል ትልቅ ሥራ ይጠብቀናል ያሉት ፕሬዝደንቱ ለዚህም የቀደሙ አመራሮች ብሎም መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡
የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ከነባር አመራሮች ሃሳብና ልምድ ተቀብሎ በዚህ መልኩ ርክክብ መፈጸም አስደሳችና አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አዲስ የመጡት አመራሮች የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚያውቁ መሆኑ በአዲስ ጉልበት መቅደም ለሚገባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ የቀደሙ አመራሮች ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው ቀጣዩ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በቅንነትና በጋራ ዓላማ መሥራት እንደሚገባ በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት