የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ከፍተኛ አመራሮች ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ታኅሣሥ 18/2017 ዓ/ም ትውውቅና በዩኒቨርሰቲው ቀጣይ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎችና የሪፎርም አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንደገለጹት የውይይት መድረኩ አዲስ በተመደቡ ከፍተኛ አመራሮችና በዩኒቨርሲቲው ማኅብረሰብ መካከል ትውውቅ ለማድረግ እንዲሁም ራስ ገዝ ከመሆን፣ ከመስክ ልይታ እና የልኅቀት ማዕከል ዘርፍን ከመለየት አንጻር እንደ መንግሥት የተቀመጡ የሪፎርም አጀንዳዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው፡፡ በተጨማሪም የአዲሱን የዩኒቨርሲቲ አመራር የትኩረትና ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ላይ ግንዛቤ መፍጠርና የጋራ መግባባት ላይ ደርሶ ወደ ትግበራ መግባት ሌላኛው የውይይት መድረኩ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ኢ/ር አብደላ በዕለቱ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሰንድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ እንዲሁም ታዋቂና ተወዳዳሪ የምርምርና የፈጠራ ማዕከል እንዲሆን እንደ መንግሥት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረው በዚሁ አቅጣጫና የመስክ ልየታ መሠረት ውኃና ምኅንድስና ቁጥር አንድ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት እንዲሁም የልኅቀት ማዕከል እንዲሆን በመንግሥት መወሰኑን አውስተዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ የየኒቨርሲቲውን ራእይ እንዲሁም የሪፎርም አጀንዳዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ያሉ ስጋቶችንና መልካም አጋጣሚዎችንም አቅርበዋል፡፡
እንደ ሀገር የተሰጡ ተልእኮዎችን፣ የመስክና የልኅቀት መስኮችን እንዲሁም በቅርቡ ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመው የቁልፍ ተግባራት ስምምነት መሠረት በርካታ የለውጥ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅብናል ያሉት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ለዚህም የሚሆኑ ስትራቴጂዎችን አዲሱ አመራር መቀየሱን አስረድተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሠራተኞች መካከል የትብብር መንፈስን ማዳበር፣ በመንግሥት የተቀመጡ የሪፎርም አጀንዳዎች ላይ ማተኮር፣ የውስጥ ቅሬታዎችን በቶሎ መፍታትና ፈጣን ምላሽ መስጠት፣ ከዕለት ተዕለት ሥራዎች ባሻገር ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት፣ ፈጣንና ውጤታማ የግዥ ሥርዓት ማስፈን፣ የተማሪዎች አገልግሎትን ማሻሻል፣ ፕሮግራሞችን፣ የምርምር ቤተ ሙከራዎች ማደራጀትና ዕውቅና እንዲያገኙ መሥራት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በሁሉም ዘርፎች ማስፋፋት እና የዩኒቨርሲቲውን ሆስፒታል በሙሉ አቅሙ ሥራ እንዲጀምር ማስቻል አዲሱ አመራር ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው መስኮች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም የየኒቨርሲቲውን ገጽታ (Visibility) በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጨመር ይሠራል ያሉት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ በዩኒቨርሲቲው ላይ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሊሠራ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡
ገለጻውን ተከትሎ የተለያዩ ጥያቄዎች በተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ለተኑሱት ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገብረማርያም፣ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እና ፕ/ር ጳውሎስ ታደሰ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ከፍተኛ አመራሮቹ በተለይ ከግብአት ጋር ተያይዘው የተነሱ ጥያቄዎችን የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት መስኮችን በተከተለ መልኩ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የሥራ ኃላፊዎቹ በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችን እንደ ግብአት በመጠቀም ቀደም ብለው ባዘጋጁት ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ላይ በማካተት ለለውጥ እንደሚተጉ አስረድተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች መድረኩ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የሪፎርም አጀንዳዎች እንዲሁም ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎችን የተገነዘቡበት መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልእኮ እንዲወጣና በሁሉም መስኮች ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣትና ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በማጠቃለያ ንግግራቸው ለውጥ ለማምጣት ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በጋራና በትብብር ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበው ያለንን አቅምና ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ዩኒቨርሲቲውን እንደ ሀገር በሚጠበቀው ቦታ ላይ ለማድረስ መትጋት ይገባል ብለዋል፡፡ የተወጠኑ የሪፎርም አጀንዳዎችን ለማሳካት በአመራሩ በኩል ከፍተኛ ቁርጠኝነት መኖሩን ያረጋገጡት ፕሬዝደንቱ መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከጎናችን ይሁን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት