የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ገንዘብ ቁጠባና ብድር ኀብረት ሥራ ማኀበር ጥቅምት 1/2018 ዓ/ም ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ጠቅላላ ጉባኤው የማኅበሩን የ2017 ዓ/ም የሥራ አፈጻጸም መገምገምና የ2018 ዓ/ም እቅድ ሪፖርት ማቅረብ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ ሥራ አስፈጻሚዎችን ማሟላት እና ሌሎች ተያያዥ አጀንዳዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ መሰለ እሸቴ ጉባኤው የማኅበሩን የ2017 ዓ/ም የፋይናንስ የሥራ አፈጻጸም መገምገም እና በቀጣይ መሻሻል በሚገባቸው ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ምክረ ሐሳብ ልውውጥ ማካሄድን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ በአባላቱ የጋራ ራእይና ፍልስፍና መመሥረቱን እና ለአባላቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ እንዲሁም ዘላቂ እድገትና ብልጽግና መረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡ አቶ መሰለ አያይዘውም ባለፈው በጀት ዓመት የአባላትን ቁጥር በማሳደግ፣ የቁጠባ ባህልን በማዳበር እና የፋይናንስ አገልግሎት አሠራርን በማሻሻል ረገድ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር የሚገጥሙ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ለማለፍና ዘመኑን የሚመጥን የቴክኖሎጂ ዕውቀትና አሠራር መከተል ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት ሰብሳቢው በ2018 ዓ/ም የአባላቱን የመቆጠብ እና የመበደር አቅም ማሻሻል፣ የሥራ አስፈጻሚዎችንና የአባላቱን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ፣ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ በዓመቱ ከታቀዱ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ እና የዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ቁጠባና ብድር ማኅበር የበላይ አመራር አቶ ሄኖክ ጌታቸው የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለመፍታት መሰል ማኅበራት አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ገንዘብ ቁጠባና ብድር ማኅበር አሁን ላይ ከ100 ሚሊየን በላይ ካፒታል በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኝና በክልሉ ከሚገኙ ማኅበራት ቀዳሚ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሄኖክ ማኅበሩ የአገልግሎት አሠራሩን በማዘመን ከኢትዮ ቴሌኮም እና በሀገሪቱ ከሚገኙ ሌሎች ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠር መሥራት የሚጠበቅበት መሆኑን ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ገንዘብ ቁጠባና ብድር ኀብረት ሥራ ማኅበር የብድር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር እንደልቡ ጎአ በበኩላቸው ቀደም ሲል በማኅበሩ በኩል ሲሰጥ የቆየውን የቁጠባ መጠን ቀድሞ ከነበረበት 3 እጥፍ ወደ 5 እጥፍ ማሳደግ፣ የበዓላት የብድር መጠን ቀድሞ ከነበረበት 3000 ብር ወደ 5000 ብር ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ለሁለት ሰው ብቻ ተገድቦ የነበረውን ዋስ የመሆን መመሪያ ለሦስት ሰዎች ዋስ መሆን የሚያስችል የአሠራር ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት