አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ውድድር በጥር 23/2017 / ውሎ በወንዶች እግር ኳስ ጨዋታ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲን 6 ለ 1 በሆነ ውጤትማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መቀላቀል ችሏል። በተጨማሪም በወንዶች አትሌትክስ በ200ሜ በተማሪ ማቤል ቱት አማካኝነት የነሐስ ሜዳሊያ እንዲሁም በ400ሜ የዱላ ቅብብል በተማሪ ማቤል ቱት፣ ዳንኤል ተፈራ፣ ያሬድ ታደሰ እና ቴዎድሮስ ጌትነት አማካኝነት ተጨማሪ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ተችሏል፡፡  ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በእግር ኳስ ጨዋታው የቡድኑን የድል ጎሎች በመጀመሪያው አጋማሽ 28 ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት እና 42 ደቂቃ የተገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ 47ው፣ 64ው፣ 69 እና 78 ደቂቃዎች በተከታታይ የቡድኑ አምበል ተማሪ ምንተስኖት ብሩክ እና ናትናኤል ንጋቱ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ተጨማሪ ጎሎችን ተማሪ አቦይ ቹዩንግ እና ሳሙኤል ባሩዳ አስቆጥረዋል፡፡

ከድሉ በኋላ የቡድኑ አሠልጣኝ / አንተነህ ዘርይሁን በሰጡት አስተያየት ቡድንትጋት በመሥራት ለስኬቱ መብቃታቸውን ገልጸው ካለፉት ጨዋታዎች ወዲህ ቡድኑ እያሳየ ያለውን መሻሻል በማውሳት ይህንን ስኬት ለማስቀጠልና ዋንጫውን ለማስጠበቅ ያላቸውን አቅምና ጽኑ እምነት ገልጸዋል። አሠልጣኙ አክለውም በዩኒቨርሲቲው በኩል እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ እና ክትትል በማድነቅ ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተማሪ ምንተስኖት ብሩክ  በእግር ኳሱ ለተገኘው ስኬት ቡድኑ ያለው ጥንካሬና ኅብረት ዋናው ምክንያት ነው በማለት በውጤቱ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል።

ውድድሩ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች እስከ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ/ም የሚቆይ ይሆናል።

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት