የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በተሻለ ስኬት ማከናወኑን አስመልክቶ ለአካዳሚክ ፣ ምርምርና አስተዳደር ሠራተኞቹ ያዘጋጀው ልዩ የምስጋና መርሐ ግብር መስከረም 9 ቀን 2019 ዓ.ም በዋናው ግቢ ስታዲየም በድምቀት ተካሂዷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጅነር አብደላ ከማል በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ንግግራቸው ያለፈው የ2018 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸው መርሐ ግብሩም ለነዚህ ስኬቶች አስተዋጽኦ ላደረጉ አካዳሚክ፣ ምርምርና አስተዳደር ሠራተኞች ልባዊ ምስጋና ለማቅረብ እና ነገን የበለጠ ስኬት ለመገንባት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዝደንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በ2019 ዓ.ም ወደ ራስ-ገዝነት (Autonomy) ከሚሸጋገሩ የሀገራችን ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ በትምህርት ሚኒስቴር ገለልተኛ ገምጋሚዎች ቡድን የዝግጁነት ግምገማ ተካሂዶ የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ተቋሙ ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ የሜትሮሎጂ ድርጅት (WMO) የምሥራቅ አፍሪካ የሜትሮሎጂ እና የአየር ንብረት ሥልጠና ማዕከል ሆኖ መመረጡንም ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከሚያሳትማቸው አምስት የምርምር ጆርናሎች መካከል አራቱ ሀገር አቀፍ እውቅና ማግኘት መቻላቸውን የገለጹት ዶ/ር ኢንጅነር አብደላ የማስተማሪያና ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ተኝቶ ህክምናን ጨምሮ አጠቃላይ የህክምና አገልግሎት በማስፋት፣ ዘመኑ የደረሰባቸውን የህክምና ቴክኖሎጂዎች በመታጠቅ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል። በሌላ በኩል በአባያ ካምፓስ የሚገኘውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ደረጃ በማሻሻል የስቴዲየሙ በ2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከሚካሄድባቸው ስቴዲየሞች አንዱ ሆኖ መመረጡ ሌላኛው በበጀት ዓመቱ የተመዘገበ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።
ፕሬዝደንቱ አክለውም የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤትን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢነት ሲመራ የቆየው የጋሞ ባይራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። በኮንሶ ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች የተገነቡ 100 የመኖሪያ ቤቶች እና በጎፋ ዞን የኬንቾ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቁ ጠቁመው በታዳሽ ኃይል፣ በንጹሕ መጠጥ ውኃ እና በሌሎች ዘርፎት ውጤታማ የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባራት መፈጸማቸውን አክለዋል።
የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጅነር ቦጋለ ገብረማርያም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ያስመዘገበው ስኬት የአካዳሚክና አስተዳደር ሠራተኞች ባደረጉት ብርቱ ጥረት የተገኘ መሆኑንና ይህንን ለማስቀጠል መርሐ ግብሩ የተሻለ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በ2018 በጀት ዓመት በመማር-ማስተማር፣ በምርምር እና በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች የተመዘገቡት አበይት ስኬቶች በርካታ ውስብስብ ተግዳሮቶችን በጽናትና በሥራ ወዳድነት በማለፍ የተገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም የዩኒቨርሲቲው የወደፊት እጣ ፈንታ ወደ ራስ-ገዝነት ከሚደረገው ሽግግር ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን በመጠቆም፣ በ2019 በጀት ዓመት በትብብር ፕሮጀክቶች፣ በዓለም አቀፍ ትስስሮች እና በጆርናሎች ጥራትና ቁጥር ላይ ከፍተኛ ጥራት ያለው የላቀ ለውጥ ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሠራ አብራርተዋል።
በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ዮሐንስ ዳና ሁሉንም የዩኒቨርሲቲ ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ ሁኔታ የተዘጋጀው መርሐ ግብር የሚደነቅና የሥራ ተነሳሽነትን የሚጨምር መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አድሮ ኦሻ እና ወ/ሮ አበራሽ በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ መርሐ ግብሩ ዩኒቨርሲቲው ለሚያስመዘግባቸው ዘርፈ-ብዙ ስኬቶች የሠራተኛው ሚና የላቀ መሆኑን ማሳያና ለቀጣይም ሊጠናከር የሚገባው መልካም ባህል መሆኑን ገልጸዋል።
በዝግጅቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ የተለያዩ አዝናኝ ስፖርታዊ ውድድሮች ተካሂደዋል። በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ማዕከል አዲስ የተቋቋመው የሙዚቃ ቡድን አዝናኝ የሙዚቃ ሥራዎችን አቅርቧል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

