በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ እና የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ያደረገ ሲሆን፣ በዚሁ መርሃ-ግብር በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ነባር ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ዕውቅና ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም ተሰጥቷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰማ በዝግጅቱ ላይ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ሴቶች ተወዳዳሪና ተሸላሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው፣ ቁጥራቸውን አሁን ካለበት ደረጃ በላይ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በትጋት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። አክለውም መርሃ-ግብሩ የሴት ተማሪዎችን አቅም ለመገንባት፣ ስኬታቸውን በማሳየት ለሌሎች አርአያ ለማድረግ እንዲሁም አዲስ ገቢዎች በቤተሰባዊ ፍቅር ወደ ትምህርት ዓለም ሰላማዊ ሽግግር እንዲያደርጉ መሠረት የሚጥል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል። የሴቶች ስኬት የሁሉም ማኅበረሰብ ዕድገት መገለጫ በመሆኑ፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በትምህርትም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው ድልን ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አዲስ ገቢ ተማሪዎችም ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን አርአያ በማድረግ እርስ በርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው፣ ዕውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎች በቆይታቸው የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች አልፈው ያስመዘገቡት ውጤት የሚያስመሰግንና የሚያሸልም ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም በሁለቱ ኢንስቲትዩቶች የሴት ተሸላሚ ተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምር ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚሰሩ ገልጸው ተማሪዎች ሕይወታቸውን የሚቀይሩበትና ለሀገራቸው ኩራት የሚሆኑበትን ታሪክ እንዲጽፉ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ ባደረጉት ንግግር፣ ከዚህ ቀደም በሀገራችን የተደረጉ ጥናቶች በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የሴቶች ቁጥር አናሳ መሆኑን ያሳዩ እንደነበር አብራርተዋል። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በተተገበሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምክንያት በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሴት ተማሪዎች ቁጥርና ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። ከፍተኛ ውጤት የጥረትና የትጋት እንጂ የፆታ ጉዳይ አለመሆኑን ያብራሩት ወ/ሪት ሰናይት ጽሕፈት ቤታቸው ተማሪዎች በሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ሁሉ ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል። ተማሪዎች በራሳቸው በመተማመን፣ በጥበብና ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ብቁና ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ አሳስበዋል።
በመቀጠልም የሁለቱ ኢንስቲትዩቶች የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ አቶ አብዮት በላይነህ ስለ መርሃ-ግብሩ ዓላማ፣ ጽሕፈት ቤቱ ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች እና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል አዲስ ስራ ላይ ስለዋለው የጥቆማ መስጫ ዌብሳይት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
በመጨረሻም ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ነባር ተማሪዎች መካከል ተማሪ ብሩክታዊት ተረፈ እና ተማሪ ፈትያ አህመድ ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን፣ ተማሪዎች ውጤታማ የጥናት ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚገባ፣ የሚያነቡትን ነገር ተረድተው ከቴክኖሎጂ ጋር ማዛመድ እንደሚያስፈልግ፣ በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዙሪያ እርስ በርስ መወያየት እንደሚገባ፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እና መልካም ጓደኞችን መምረጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከቀድሞ ተማሪዎች ተሞክሮ መውሰድ እና ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል በትጋት መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

