የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝትና የኢንደስትሪ ትስስር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን ለተወጣጡ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች የእንስሳት እግርና አፍ በሽታን (Bovine Foot & Mouth Disease) ሥርጭትና መቆጣጠሪያ ዘዴ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሚያዝያ 2/2017 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በኮሌጁ የተከናወነ የምርምር ሥራን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ የእንስሳት የእግርና አፍ በሽታ በስፋት እየተሰራጨ ያለና በርካታ የጋማ ከብቶችን የሚጎዳና ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ሲሆን ሥልጠናው የምርምር ውጤትን ወደ ማኅበረሰቡ ለማሻገር የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው ከዞኑ ጋር በዘርፉ በትብብር ለመስራት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደግፌ በዘርፉ ላይ በትብብር መስራት በበሽታው ምክንያት የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል፡፡
የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ዓለማየሁ ወርቁ በጥናቱ የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረው ትምህርት ክፍሉ ከእንሰሳትና ዓሳ ኃብት ምርምር ማዕከል ጋር በመሆን መሠል በሽታዎች ላይ ጥናት በማካሄድ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ዋሲሁን ስዩም ጥናቱ በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ገረሴ እና ጨንቻ ወረዳዎች ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረው በዞኑ ውስጥ 26.8 ከመቶ የበሽተው ሥርጭት መኖሩ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ በሽታው ከብቶችን፣ ፍየሎችንና በጎችን እንደሚያጠቃና በተለያዩ መንገዶች እንደሚተላለፍ የሚገልጹት ተመራማሪው ምርትና ምርታማነትን በመቀነስ ኢኮኖሚን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ለማኅበረሰቡ በበሽታው ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሰራቱን የገለጹት ዶ/ር ዋሲሁን ከአምስት ሺህ በላይ ለሆኑ እንስሳትም ክትባት መሰጠቱን አውስተዋል፡፡ የበሽታው መኖር ሀገሪቱ በመስኩ ማግኘት የሚጠበቅባትን ጥቅም እንዳታገኝ የሚያደርግ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በእንስሳት ጤና ሳይንስ ትምህርት ክፍል የእንስሳት ሕክምና መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ኤፍሬም ቶራ በሽታው ድንበር ተሻጋሪ መሆኑን ጠቅሰው ለኅብረተሰቡና ለባለሙያዎች ግንዛቤን በመፍጠር በሽታውን ለመቆጣጠርና ለመግታት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሽታውን በክትባትና ያለክትባት እንዴት መግታት እንደሚቻል፣ የክትባት ስልቶችና ዘዴዎች በሥልጠናው መዳሰሳቸውን ዶ/ር ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡
በጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳት ጤና ዘርፍ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ጸጋለም ኃ/ሚካኤል በሽታው ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ከቀረበው የጥናት ውጤት መገንዘብ እንደተቻለ ገልጸው በሽታው ምርትና ምርታማነትንና የሀገርን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ በቀጣይ የመከላከል ሥራው ላይ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው ለመሥራት ጥሩ ግንዛቤ ማዳበራቸውን ተናግረዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት