አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን በሚያደርገው ጉዞ የዩኒቨርሲቲውን ሴኔት መተዳደሪያ ደንብ እና ስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ ለማከናወን ኅዳር 3/2017 ዓ/ም የማስጀመሪያ መር ግብር አካሂዷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ በ2019 የትምህርት ዘመን ከምደባ ወደ ቅበላ ለመሻገር ማቀዱን ገልጸዋል። ለዚህም ዋነኛ የዝግጅት አካል የሆነውን የሴኔት መተዳደሪያ ደንብ እና ስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማጠናቀቅ የተለየ ትጋትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።

ክለሳውን ለማከናወን ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተዋቀሩ 21 አባላት ያሉት የስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳ እና 11 አባላት ያሉት የሴኔት መተዳደሪያ ደንብ ክለሳ ኮሚቴዎች የተቋቋሙ ሲሆን በኮሚቴዎቹ የሚሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደር ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ቤታ ፀማቶ ገለጻ አድርገዋል።

እንደ ዶ/ር ቤታ የዝግጅት ምዕራፉን ጨምሮ ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የታቀደ ሲሆን መረጃ መሰብሰብ፣ ማጠናቀር፣ በአማካሪ ካውንስል አስገምግሞ አስተያየቶችን ማካተት እና ሌሎች አስፈላጊ ሂደቶች ሲጠናቀቁ የተከለሰው የሴኔት መተዳደሪያ ደንብና ስትራቴጂክ ዕቅድ ለፌዴራል አማካሪ ቦርዱ የሚላክ ይሆናል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በተያዘው ዕቅድ መሠረትም ጥር 7/2017 ዓ/ም ከሌሎች ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲውዎች ጋር በፌዴራል መድረክ የሚቀርብ መሆኑን ዶ/ር ቤታ ገልጸዋል።

ገለጻውን ተከትሎ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የክለሳ ሥራው የጊዜ ሰሌዳ ማጠር፣ የኮሚቴ አባላት ሌሎች ተቋማዊ ሥራዎች ጫና ያለባቸው መሆን፣ የመረጃ አሰባሰብ፣ የከፍተኛ ትምህርት ሀገራዊ ሁነቶችና አዳዲስ መመሪያዎች እንዲሁም ተማሪ ወዶና መርጦ እንዲመጣ መሬት ላይ ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ከተሳታፊዎች ከተነሡ ሃሳቦች መካከል ይጠቀሳሉ።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት