‹‹ብርታት ጀነሬሽን›› ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከ‹‹አብሪ ማይንድ›› እና ‹‹በርቺ›› ከተሰኙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ‹‹በዛሬ ማንነታችን ነጋችንን እንሥራ!›› በሚል ርእስ ኅዳር 1/2017 ዓ.ም በሱስ አስከፊነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መር ግብር አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ለአካባቢው ወጣቶች ከሥነ ባሕርይና ሥነ ምግባር ጋር የተገናኙ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ እንደቆየ ጠቁመዋል፡፡ ከብርታት ጀነሬሽን ጋር በመተባባር ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተሰጠው የግንዛቤ መስጫ መር ግብር ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከአልኮል መጠጥና ሌሎች ሱሶች ነጻ ሆነው በትምህርታቸው እንዲጎብዙና ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ 

የብርታች ጀነሬሽን መሥራችና ማኔጀር ዮናዳብ ግርማ የመር ግብሩ ዋነኛ ዓላማ ከ21 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችን አልኮል መጠጥ እንቢ እንዲሉ በማስቻል በዓላማ የሚመራ ባለ ራእይ ትውልድ ማፍራት ነው ብለዋል፡፡

የአብሪ ማይንድ መሥራችና ማኔጀር ወ/ሮ ሀና ኃይሉ ወጣቶች ወደ ስኬት ለመድረስ ከተለያዩ ሱሶችና ከአልኮል መጠጦች መራቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ስኬት ለመድረስ ወዴት እንደሚሄዱ፣ ከየት እንደተነሱና የት ለመድረስ እንዳለሙ፣ አሁን ላይ የት እንዳሉና የመጡበት መንገድ ምን እንደሚመስል ማወቅ እንዳለባቸውና ይህም የነገ ስኬታቸውን እንደሚወስን ገልጸዋል፡፡
የብርታት ጀነሬሽን አምባሳደር አርቲስት ሸዊት ከበደ ባስተላለፈችው መልእክት ከሱስ የሚጎድል እንጂ የሚተርፍ ምንም ነገር እንደሌለ ተናግራ በተለይ ከ21 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊ ወጣቶች ወደ ሱስ ውስጥ ሲገቡ መላ ሕልውናቸውን እንደሚያጡ ተናግራለች፡፡

በመሰል ጉዳዮች ላይ ለወጣቶች ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚታወቁት የዩኒቨርሲቲው ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ በበኩላቸው በአብዛኛው ወደ ስህተት የገባንበት መንገድ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ከስህተታችን ተምረን ከተመለስን ጥሩ ሰው መሆን እንችላለን ብለዋል፡፡ በጎ ነገር የሚፈልቀው ከበጎ ሕሊና ነው ያሉት አቶ መርክነህ በጎ እሳቤ እንዲኖረን አንጎላችንን ከተለያዩ ሱሶች መጠበቅ መቻል አለብንም ብለዋል፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ሰዎች እየጠፉ ያሉት በገዛ ምርጫቸው በመሆኑ ምርጫን በማስተካከል ሕይወትን ማስተካከል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ለተማሪዎች ልምዱን ያካፈለው ወጣት ሙጡ ማዜ ወደ ሱስ ዓለም የገባው በ18 ዓመቱ እንደሆነና ከሱስ ያተረፈው ምንም ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ በሱስ ምክንያት ራሴንና ቤተሰቤን አጥቻለሁ የሚለው ወጣት ሙጡ የዕድሜውን ግማሽ በእስር ማሳለፉንም ተናግሯል፡፡ ተማሪዎች የሱስን አስከፊነት ከእኔ ተምራችሁ ከማንኛውም ሱስ የጸዳችሁ በመሆን ራሳችሁን፣ ቤተሰባችሁን እንዲሁም ሀገራችሁን የምትጠቅሙ ሆኑ ሲልም መክሯል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት