አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት እና ከሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሀገራዊ የግብርና ናሙና ቆጠራ ለማካሄድ ከዞንና ወረዳዎች ለተወጣጡ ሠልጣኞች ከነሐሴ 17/2016 - መስከረም 5/2017 ዓ/ም የሚቆይ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ መንግሥታዊ እና ሀገራዊ ተልእኮዎችን ለማስፈጸም በዩኒቨርሲቲው በኩል በርካታ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸው ይህን ሥልጠና ማስፈጸም ሀገራዊ ኃላፊነትና ግዴታም ጭምር ነው ብለዋል፡፡ ሀገራዊ ዕቅዶች የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ወሳኝ ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ የሚሰበሰበው መረጃ እንደ ሀገር የምንመራበትን ዕቅድ ለማውጣት የሚረዳ ብሎም ተመራማሪዎች ለሚያደርጉት ምርምር ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው የሚያግዝ በመሆኑ በጥንቃቄ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ ሠልጣኞች፣ አሠልጣኞችና ሱፐርቫይዘሮች በተቋሙ በሚኖራቸው ቆይታ ማግኘት ስላለባቸው አገልግሎት፣ ግዴታዎችና የግቢው አጠቃላይ የሥነ ምግባር መመሪያ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የግብርና ናሙና ጥናት ሀገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳይና የወደፊት አቅጣጫ የሚጠቁም መሆኑን ዶ/ር ደግፌ ገልጸዋል፡፡

መሰል የቆጠራ ሥራ ከ22 ዓመት በፊት መሠራቱን ያስታወሱት በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአርባ ምንጭ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስሜነህ አንበሴ ቆጠራ ለማካሄድ ከዞንና ወረዳዎች 1,650 መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሠልጣኞች መቅረባቸውን እና ከሥልጠናው በኋላ ሠልጣኞቹ የአገዳ፣ ቋሚና ጊዜያዊ ሰብሎችን የተመለከተ መረጃ ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ በታብሌት እንደሚመዘግቡ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም አሠልጣኞቹ ልምድ ያላቸውና የሦስት ዙር ሥልጠና የወሰዱ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ አስፈላጊ መረጃ የሚሰበስብ ሲሆን መረጃው ጂዲፒ/GDP/ ለመከለስ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች ለማቅረብ እንዲሁም ለተመራማሪዎች የሚረዳ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት