በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውኃ ሀብት ምርምር ማዕከል አሜሪካ ከሚገኘው "WSSC" የተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር ከሐምሌ 28-29/2017 ዓ/ም   "Understanding and Managing Disinfection Byproducts (DBPS) in Drinking  Water"  በሚል ርእስ ዓለም አቀፍ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አጠባበቅ ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት አካሂዷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ዩኒቨርሲቲው በውኃ ሀብት ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የማኅበረሰቡን የውኃ ፍላጎት ጫና ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን ገልጸው ውኃ ከማኅበረሰቡ የጤና አጠባበቅ ጋር ትስስር ያለው በመሆኑ በትብብር የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡ ዐውደ ጥናቱን ላዘጋጁት የኢንስቲትዩቱና የምርምር ማዕከሉ አመራሮች እንዲሁም ለመምህራንና ለተመራማሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰሜ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከምሥረታው ጀምሮ "የውኃ ሀብት ለሀገራችን መበልጸግ" በሚል መርሕ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ሰፊ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል። ዶ/ር ታምሩ አያይዘውም የአየር ንብረት ለውጥንና የሃይድሮፓወር አቅምን በማሻሻል፣ የታዳሽ ኃይልን እና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በማሳደግ እንዲሁም የውኃ ሀብት በማልማትና ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሀገሪቱ አሁን ላይ ለምትገኝበት የእድገት ደረጃ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት ተችሏል ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የውኃ ሀብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ኤልያስ ገበየሁ በውኃ ሀብት አጠቃቀም እና ንጽሕናውና ጤንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውኃ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት (WHO) ስታንዳርድ አንጻር በምርምር የተደገፈ ምክረ ሐሳብ ለመለዋወጥ ዐውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም ዐውደ ጥናቱ ለተመራማሪዎች ዓለም አቀፍ የምርምር አጻጻፍ ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው ብለዋል።

በ‹‹WSSC›› የንጹሕ መጠጥ ውኃ ማኔጀርና ተመራማሪ ዶ/ር ጀግናው እሳቱ ለመጠጥ ውኃ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ውኃ ወለድ በሽታዎች በርካታ ሰዎችን ለሞት እየዳረጉ መሆኑን ተከትሎ ክስተቱ ዓለም አቀፍ ስጋት ደቅኗል ብለዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውኃው ዘርፍ ቀዳሚ እንደመሆኑና የውኃ ምርምር ማዕከሉ በበቂ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ግብአት የተደራጀ በመሆኑ ተባብሮ ለመሥራት ምርጫቸው እንደሆነ ዶ/ር ጀግናው ተናግረዋል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት ስታንዳርድ መሠረት ለማኅበረሰቡ የሚሰራጭ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እና ለአገልግሎቱ የሚውሉ የውኃ ታንከሮች፣ ገንዳዎች፣ ቱቦዎች እና ሌሎች ግብአቶች ደኅንነትና ጥራት የተጠበቀ መሆን ያለበት ሲሆን ውኃን ለማከም የሚጨመረው ክሎሪን መጠንም ሳይንሳዊ ሂደትን የተከተለ ሊሆን ይገባል።

በዐውደ ጥናቱ የኢንስቲትዩቱና ምርምር ማዕከሉ አመራሮችን ጨምሮ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም የአስተዳደር ሠራተኞችና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። በዘርፉ እየተከናወኑ ለሚገኙ ሥራዎች እና በቀጣይ የሚኖረውን ትብብር አስመልክቶም ዕውቅናና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት