የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት የ2018 ዓ/ም 1ኛ ሩብ ዓመት የወላጆች ጉባኤ ጥቅምት 22/2018 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በ2017 ዓ/ም የተከናወኑ ተግባራት እና ያጋጠሙ ችግሮች በተለይ ከተማሪዎች ውጤት መሻሻል ጋር ተያይዞ ዞናዊ፣ ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12 ክፍል ተማሪዎች ውጤት እንዲሁም የወርሃዊ ክፍያ ማሻሻያ መደረጉ በውይይቱ የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ተማሪዎችን ከታችኛው እርከን ጀምሮ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረው ውይይቱ በትምህርት ቤቱ ያሉ ችግሮችንና ቀጣይ ሥራዎችን የለየንበት ነው ብለዋል፡፡ ለትምህርት ቤቱ እድገት የወላጆች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ መሥራት እንደሚስፈልግም ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ተማሪዎችን ለስኬት ለማብቃት በተለይም መምህራን በውጤት ደከም ያሉትን ለይተው ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረው የመምህራኑ ልፋት ውጤታማ እንዲሆን ወላጆችም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ከታች ከማቆያ ጀምሮ ተማሪዎችን አብቅቶ ለዩኒቨርሲቲ ማድረሱ ለየት ያደርገዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ተማሪዎች የግል ጥረትና ትጋታቸውን ጨምረው መልካም አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም ለስኬት እንዲበቁ አሳስበዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝትና የኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በዚህ ዓመት ትምህርት ቤቱን በሪፎርም ለመቀየር በታቀደው መሠረት ዲጂታል መታወቂያ ዝግጅት፣ የተማሪዎች ኦንላይን ክፍያ ሥርዓት እና የe-Learing ትምህርት ሥርዓት ተጀምሯል፡፡ ዕቅዱን በስኬት ለመፈጸም ወላጆች ከትምህርት ቤቱ ጋር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ቶሌራ ተናግረዋል፡፡ 

የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በ2017 የትምህርት ዘመን የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በ2018 ዓ/ም ዞናዊ፣ ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ውጤት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ትምህርት ቤቱን ለማዘመን የተጀመሩ ጅማሬዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ወላጆች ልጆቻቸውን በመደገፍና በመከታታል የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የወላጆችና የመምህራን ጥብቅ ግንኙነት፣ የወላጆች ድጋፍና ክትትል፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና ሌሎችም ሃሳቦችን አንሥተዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት