በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሥር የሚገኘው ‹‹የአርባ ምንጭ የሥነ ሕዝብና የጤና ምርምር ማእከል›› በአርባ ምንጭ ከተማ የሚከናወን የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት ሥርዓት/Urban Health and Demographic Surveillance System/ ይፋ አድርጓል፡፡ ማእከሉ በአርባ ምንጭ ከተማ ላይ በተመረጡ ሰባት ቀበሌያት ለሚያደርገው ጥናትም ለመረጃ ሰብሳቢዎች፣ ለመረጃ ሰብሳቢ ተቆጣጣሪዎችና ለመረጃ አስተዳደር ሠራተኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ የጥናትና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርይሁን ዘርዶ ለሀገሪቱ የጤና ሴክተር ወሳኝ የመረጃ ምንጭ ከሆኑ የሥነ ሕዝብና የጤና ምርምር ማእከላት አንዱ የኮሌጁ ማእከል መሆኑን ጠቅሰው ማእከሉ ከዚህ ቀደም በገጠሩ አካባቢ ብቻ ሲሠራ መቆየቱንና ከተማውን ለማካተት ያለመ ሥርዓት ይፋ ማድረጉ የሚያስደስት እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታተሙ ኅትመቶች/Articles/ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከኅትመቶቹ እንዲወገዱ ለሚደረጉ ጥናቶች እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ የመረጃ ጥራት እና የጥናት ሥነ ምግባር ዋነኞቹ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ በመሆኑም በማእከሉ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ጥራታቸውን የጠበቁና የታለመላቸውን ግብ የሚያሳኩ እንዲሆኑ ሠልጣኞች በትኩረትና በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

የማእከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር መስፍን ቆቴ ማእከሉ ከዚህ ቀደም በአርባ ምንጭ ዙሪያ እና ጋጮ ባባ ወረዳዎች በሚገኙ ዘጠኝ ቀሌያት የሥነ ሕዝብና ጤና መረጃዎችን በማጥናት ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ሥራው በገጠር ክፍል ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርና ከተማውን በማካተት የተሟላ መረጃ ማድረስ እንዲቻል የከተማ የጤና እና ሥነ ሕዝብ ጥናት ሥርዓት ይፋ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በመረጃ ማሰባሰብ ሒደቱ በአርባ ምንጭ ከተማ የተመረጡ ሰባት ቀበሌያት የተካተቱ ሲሆን በቀበሌያቱ ከሚገኙ እያንዳንዱ  ቤቶች ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ስደት፣ የእርግዝና ሁኔታን የሚገልጹ ወሳኝ ኩነቶች፣ ግለሰባዊ መረጃዎች እንዲሁም ሌሎችም የሥነ ሕዝብና የጤና መረጃዎች የሚመዘገቡ ይሆናል፡፡ በጥናቱ የሚገኘው መረጃ በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እና በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሚዘጋጁ ፖሊሲዎችና ዕቅዶች በግብአትነት እንደሚያገለግሉ ዶ/ር መስፍን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ለመረጃ ሥራው የተዘጋጁ መጠይቆች በታብሌት በጥንቃቄ ተሞልተው ‹‹Open HDS›› እና ‹‹ODK›› ሶፍትዌሮች ላይ የሚገቡ ሲሆን ሥልጠናው የሚሞሉ መረጃዎችና አሞላላቸው እንዲሁም ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ላይ ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡ በክፍል ውስጥ ያለውን ሥልጠና ሲያጠናቅቁም የተግባር ልምምድ የሚያደርጉ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት