አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "Digital Financial Literacy Campaign" በሚል ርእስ ለዩኒቨርሲቲው ሴት የአስተዳዳር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እና ለተማሪዎች በዲጂታል ፋይናንስ ሊትረሲ ዙሪያ ከታኅሣሥ 7-8/2017 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ፋይናንሻል ሊትረሲ ሥልጠና አስተባባሪ ወ/ሮ ጥሩ ቤዛ በአሁኑ ወቀት ዲጂታል ፋይናንስ በሀገራችን በገጠሩም ሆነ በከተማ ተደራሽ እየሆነ ያለ ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪዋ ሥልጠናው ከዚህ ቀደም ታዳጊ ልጆችና ወጣቶች ወላጆቻቸውን እንዲያነቁ በማሰብ ለ2ኛ ደረጃ እና ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተማሪዎች የተሰጠ ሲሆን የዩኒቪርሲቲ ተማሪዎች ቴክኖሎጂው በእጃቸው ያለ በመሆኑ ከጥንቃቄ ጉድለት ለአጭበርባሪዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር ሥልጠናው ተሰጥቷቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የኮምፕዩቲንግ እና ሶፍትዌር ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር የሆኑት አሠልጣኝ ዶ/ር ክብረአብ አዳነ ሥልጠናው ‹‹Introduction to Digital Finance››፣ ‹‹‹Identifying & Avoiding Fraud›› እና ‹‹Digital Ethiopia learning Platform›› በሚሉ ይዘቶች መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ የመረጃ መረብ አጠቃቀማችን ጥንቃቄ የተሞላ አይደለም ያሉት አሠልጣኙ ሥልጠናው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ዐውቀን ራሳችንን ከአጭበርባሪዎች ለመጠበቅ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የብቃትና ሰው ሀብት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምነሽ ሕዝቅኤል ለረዥም ጊዜ ተመሳሳይ የኮምፕዩተር ይለፍ ቃል እንደሚጠቀሙ አስታውሰው ከሥልጠናው የይለፍ ቃል አጠቃቀምና ሌሎችም ጠቃሚ መረጃዎችን እንዳገኙ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪካልና ኮምፕዩተር ምኅንድስና ተማሪ ምሕረቱ ሙሉነህ በበኩሉ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ሳናጣራ ለሌላው ማጋራትም ሆነ ለአጭበርባሪዎች መጋለጥ እንደሌለብን ከሥልጠናው ተረድቻለሁ ብሏል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት