አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከባለድርሻ አካላትና ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ በተገበረው "ECoD" ፕሮጀክት ያስገነባውን መንገድ ያስመረቀ ሲሆን ሥራው መጠናቀቁን አስመልክቶ የካቲት 14/2015 ዓ/ም የምክክር መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ዩኒቨርሲቲው በመሎ ኮዛ ወረዳ ፕሮጀክት ቀርጾ በጀት በመመደብ እንዲሁም በወረዳው መንግሥትና በማኅበረሰቡ ትብብር በትምህርት፣ በግብርናና በጤናው ዘርፍ ትልቅ ሚና ያለው የመንገድ ዝርጋታ ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል። በዚህም በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የኑሮ ሁኔታ እና የተማሪዎችን ውጤታማነት ማሻሻል በሚቻልበት ሁናቴ በቂ የጥናትና ምርምር እና የትግበራ ሥራ ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ቤታ ጻማቶ ፕሮጀክቱ 1.75 ሚሊየን ብር ወጪ ማይዘሎ፣ ቦክሬ፣ ቶባ፣ ዳላና ሌሎች የመሎ ኮዛ ወረዳ ገጠር ቀበሌያን በመንገድ የሚያስተሳስር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹መንገድ ለማኅበረሰቡ እድገት መሳለጥ ቁልፍ ሚና አለው›› ያሉት ዶ/ር ቤታ የትምህርት ጥራት እና የማኅበረሰቡን ጤና ማሻሻል እንዲሁም የግብርና ምርታማነት መጨመር ዓላማ በማድረግ በተመረጡ የወረዳው ት/ቤቶች ለሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ለአርሶ አደሮች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ት/ቤት ተመራማሪዎች ብርቱ ጥረት ፕሮጀክቱ የተከናወነ መሆኑንም ዶ/ር ቤታ አክለዋል፡፡
የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉነህ አውሳቶ ዩኒቨርሲቲው ወረዳው ያለበትን የመንገድ ተደራሽነት ተግዳሮት ለመፍታት የሠራው ሥራ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸው የወረዳውን መንግሥትና ኅብረተሰቡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የሚያከናውናቸውን የጥናትና ምርምር ተግባራት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ቶባ አልቡጫ 1ኛና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ደርሶ ደገፉ ዩኒቨርሲቲው የት/ቤቱን መምህራንና ተማሪዎች አቅም ለማሻሻል ባከናወናቸው ተግባራት የተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎና ውጤት እየተሻሻለ መምጣቱን እንዲሁም ት/ቤቱ በ2017 ዓ/ም የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል መሻገር የሚያስችል ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸው ጥሩ ምሳሌ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የትምህርት ጥራት እና የግብርና ምርታማነትን ማሻሻልን መነሻ በማድረግ በ2014 ዓ/ም ተጀምሮ በ2018 ዓ/ም በተጠናቀቀው የመንገድ ግራንት ፕሮጀክት ሃሳብ በማመንጨትና መሪ ተዋናይ ለሆኑ ባለድርሻ አካላት የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው አመራርና ተመራማሪዎችን ጨምሮ የመሎ ኮዛ ወረዳ፣ የላሃ ከተማ አስተዳደር፣ የጎፋ ዞን፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካላት እንዲሁም የሃይማት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በመርሐ ግብሩ ተሳትፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





