በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና በዓለም አቀፉ የጄኔቲክ ኢንጂነሪንግና ባዮቴክኖሎጂ ማዕከል (ICGEB) በጋራ የሚተገበረውና በጣሊያን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው  የባዮቡስት (BioBoost) ፕሮጀክት፤ በጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ሆሎኦ ቀበሌ በዘመናዊ የእንሰት እርሾ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ ለአካባቢው አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና የቀበሌ አመራሮች በተግባር የተደገፈ የአቅም ማጠናከሪያ ስልጠና ሐምሌ 10/2018 . ሰጥቷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝትና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር / ቶለራ ሴዳ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በፍትህ እና በግብርና እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ማህበረሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ ጉድኝት ተግባራትን በቅንጅት እያከናወነ ይገኛል። በተለይም ላለፉት አስርት ዓመታት የተከናወነው የእንሰት ምርምር ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለና ለብሄራዊ ፖሊሲ ትኩረት ያስገኘ ስኬታማ ተግባር መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ወቅትም በምርምር የተገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ አርሶ አደሩ ለማሰራጨት ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ እና የዩኒቨርሲቲው የባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪ / አዲሱ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በጣሊያን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እና በዓለም አቀፉ የጄኔቲክ ኢንጂነሪንግና ባዮቴክኖሎጂ ማዕከል (ICGEB) አጋርነት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት እየተተገበረ የሚገኝ መሆኑን አብራርተዋል። ዋና ትኩረቱም በቤተ-ሙከራ የበለጸገውን ዘመናዊ የእንሰት እርሾ ማስተዋወቅና ማሳደግ ላይ መሆኑን የገለጹት / አዲሱ፣ በዩኒቨርሲቲው የተከናወኑ የምርምር ተግባራት የእንሰት አመራረትንና ማቀነባበሪያ ስርዓትን በማዘመን ምርቱን እስከ ውጭ ሀገር ኤክስፖርት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ መሰረታዊ ለውጦችን ማምጣታቸውን ጠቁመዋል።

 አያይዘውም ዩኒቨርሲቲውና አጋር ድርጅቶች እስከ አሁን ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ 46 ዘመናዊ የእንሰት ማቀነባበሪያ ጣቢያዎችን ወይም የእንሰት መፍጫ ቤቶችን መገንባታቸውን አስታውሰው፣ እስከ 2026 . መጨረሻ ድረስ የጣቢያዎቹን ቁጥር 100 ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። ይህ ተግባር ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣  የምግብ ጥራትን ለመጠበቅና የምርት ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘፍኔ ዛዳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲውና አጋር አካላት የእንሰት ሰብልን ለማዘመን እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ ጥረት አድንቀዋል። የእንሰት ሰብል የአካባቢው ማህበረሰብ የጀርባ አጥንትና ከምግብም በላይ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ መንግስት ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ውጥኖችን በመቅረጽ በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተግባር ላይ እንዲያውሉት አሳስበዋል።

ከዕለቱ አሰልጣኞች መካከል የባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪው አቶ አውቀ ማሞ በበኩላቸው፤ ባህላዊው የእንሰት አመራረት እና ማብላላት ሂደት ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ፣ ዘመናዊ መሣሪያዎች የሌሉበት እና ረጅም ወራትን የሚወስድ መሆኑን አስገንዝበው፣ ዩኒቨርሲቲው ለእነዚህ ችግሮች እንደ የእንሰት መፋቂያ ማሽኖችና ዘመናዊው የእንሰት እርሾን ጨምሮ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ያካተቱ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን ይዞ መቅረቡን አሳይተዋል።

ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት ሰልጣኞቹ / ገነት ዶኪሌ እና / ሰላምነሽ ጌታቸው እንደተናገሩት፤ ስልጠናው በተለይ ቀደም ሲል እንሰትን ለመፋቅ እና ለማብላላት ይወስድ የነበረውን ረጅም ወራትና አድካሚ የሴቶች ጉልበት በዘመናዊ ማሽኖችና በሳይንሳዊ እርሾ በመተካት ትልቅ እፎይታን የሚያመጣ ነው። ቴክኖሎጂው የምግብ ብክነትን በማስቀረት በጥቂት ቀናት ውስጥ ንጹህ ቆጮ ለገበያና ለቤት ፍጆታ ለማቅረብ እንደሚያስችላቸው የገለጹት ሰልጣኞቹ፣ ያገኙትን እውቀት ወደ ቀያቸው ሲመለሱ በተግባር ላይ ለማዋልና ለሌሎች አርሶ አደሮችም ለማጋራት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ሆሎኦ ቀበሌ የተሰጠው ይህ የአቅም ግንባታ ስልጠና፤ እነዚህን የፕሮጀክቱን ዘላቂ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግቦች በቀጥታ ወደ መሬት በማውረድ የአካባቢውን ማህበረሰብ የእንሰት ማብላላት ባህል እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅም ለመቀየር የተወጠነ የክህሎት ሽግግር አካል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ መሰል ሥልጠናዎች በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚሰጡ ከፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት