በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚተገብረው የ "JOB-FEET" (Job Opportunity for Female Employability through the Adoption of Proven Enset Technologies) ፕሮጀክት፣ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ወይዛ ቀበሌ ያቋቋመውን በዞኑ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የእንሰት ምግብ ማቀነባበሪያ ማዕከል ወይም የእንሰት ወፍጮ ቤት ትናንት ኅዳር 5 ቀን 2019 ዓ/ም በይፋ ሥራ አስጀምሯል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ከማዕከሉ መቋቋም ጋር ተያይዞም፣ በአካባቢው ለተደራጀው አዲስ የ "ብርቱ የእንሰት ምግብ ማቀነባበሪያ ማህበር" 30 አባላት ለአራት ተከታታይ ቀናት የቆየ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ተሰጥቷል። በስልጠናውም የማህበሩ አባላት በዘመናዊ የእንሰት መፋቂያና መጭመቂያ ማሽኖች አጠቃቀም፣ በዘመናዊ የማብላላት ቴክኒኮች እና በእርሾ አጠቃቀም ዙሪያ በቂ ክህሎት እንዲጨብጡ ተደርጓል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ሰብሳቢ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል፣ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ የዞኑና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተገኝተዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል፤ ዩኒቨርሲቲው የእንሰትን ሰብል አጠቃቀም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየለወጠውና ዘመናዊ እያደረገው እንደሚገኝ ገልጸዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ዩኒቨርሲቲው እና በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎቹ ላከናወኗቸው የላቁ የፈጠራ ስራዎች እስካሁን ድረስ በርካታ ሀገር አቀፍ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ እውቅናዎችንና ሽልማቶችን ማግኘቸውን ፕሬዝደንቱ አብራርተዋል። አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እስከ አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ 50 ዘመናዊ የእንሰት ማቀነባበሪያ ማዕከሎችን ወይም የእንሰት ወፍጮ ቤቶችን ማቋቋሙን ጠቅሰው፣ እነዚህ ማዕከላት በተለይም ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የ "JOB-FEET" ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በጠንካራ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶችና ፈጠራዎች ላይ ተመስርቶ በሶስት ክልሎች ተግባራዊ እየሆነ ያለ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብን የማገልገል ስራውን በቀጥታ ከሚገኝበት አካባቢ ባለፈ፣ በሌሎች ማህበረሰቦችም ጭምር በማዳረስ ሰፊ ተደራሽነትን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ይህ ፕሮጀክት ማሳያ መሆኑን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ከአጋሮቹ ጋር በመሆን እንሰት ላይ እስካሁን የሰራቸው ሥራዎች እጅጉን ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ በቀጣይም ሥራውን ይበልጥ በማስፋት እንሰት ከአገር ውስጥ አልፎ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ የትብብር ሥራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ በበኩላቸው አሁን ላይ ፕሮጀክቱ 90 በመቶ የሚሆነውን አፈፃፀም ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል። የፕሮጀክቱ ለጋሽ አካላትና ነፃ ገለልተኛ ገምጋሚዎች በእስካሁኑ የፕሮጀክቱ ውጤትና አፈፃፀም እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በቀጣይም ፕሮጀክቱን በሁለተኛው ምዕራፍ ለማስፋትና ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አብራርተዋል።
አዲስ በይፋ ሥራ የጀመረው የእንሰት ምግብ ማቀነባበሪያ ማዕከል በጎፋ ዞን የመጀመሪያው መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ወንድወሰን፣ በዞኑ ከዚህ ቀደም በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ከበሽታ ነፃ የእንሰት ችግኞች ማባዛትና መሸጥ ስራ ላይ ብቻ 5 ማህበራት መደራጀቸውን እና አሁን ላይ እነዚህ ማህበራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በሲዳማ ክልሎች ለ1,500 ዜጎች ቀጥተኛ የስራ እድል ለመፍጠር ያለመ ሲሆን፣ በዋናነት ከበሽታ ነፃ የሆኑ የእንሰት ችግኞች ማባዛት፣ የእንሰት ምግብ ማቀነባበር፣ የእንሰት ማቀነባበሪያ ማሽኖች ማምረት እና ከእንሰት ቃጫ የተለያዩ ጌጣጌጦች ማምረት በሚሉ አራት የትኩረት መስኮች ላይ ማኀበራትን በማደራጀት የሥራ እድል እየፈተጠረ እንደሚገኝ ዶ/ር ወንድወሰን ገልጸዋል።
በማህበሩ ስም ሃሳባቸውን ያቀረቡት የማህበሩ አባል ወ/ሮ አበበች ጥላሁን በበኩላቸው እነዚህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የጉልበት ሥራን በእጅጉ እንደሚቀንሱ፣ ጊዜን እንደሚያድኑ እና ጥራት ያለው ምርት ለማምረት የሚያስችሉ እጅግ ድንቅ መሆናቸውን ገልጸዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን እና የፕሮጀክት አስተባባሪዎችን ይህንን የለውጥ አብሳሪ ቴክኖሎጂ ወደ አካባቢያቸው በማምጣታቸው አመስግነው በማህበራቸው በኩል ጠንክረው በመስራት ውጤታማ ለመሆን ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በአውሮፓ ኅብረት (EU) እና በጀርመን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በሚተገበረው «ስኪልስ ኢኒሼቲቭ ፎር አፍሪካ» (SIFA) መርሐ ግብር እና በአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ (AUDA-NEPAD) አስተባባሪነት የሚደገፈው ይህ «JOB-FEET» ፕሮጀክት፤ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋና ፈጻሚነት እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ፖሊቴክኒክና ሳተላይት ኢንስቲትዩት እና ከሉሲ እንሰት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (Lucy Enset PLC) ጋር በመተባበር እየተከናወነ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

