አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአልባስተር ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር ያቋቋመው ዘመናዊ የእንሰት ቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ድጋፍ የሚሠራ የእንሰት ሞባይል መተግበሪያ ጥቅምት 22/2018 ዓ/ም በይፋ ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንሰት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚችል ተክል ሲሆን ዩኒቨርሲቲው እንሰት ጋር የተገናኙ በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በትብብር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪ መቋቋም አርሶ አደሩ ከበሽታ የጸዱ ችግኞችን በብዛት እንዲያገኝ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ እንደሆነም ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ተናግረዋል። የዚህ ዓይነት ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ አቅሞችን መፍጠር መቻል እንደ ተቋም ትልቅ ስኬት ከመሆኑ ባሻገር ዘርፍ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው አንስተዋል።
በተጨማሪም በትብብር ፕሮጀክቱ የበለጸገው የእንሰት ሞባይል መተግበሪያ ለእንሰት አምራች አርሶ አደሮች ተጨማሪ ጥቅሞችን የሚያስገኝና እንሰትን በሌሎች የሀገሪቱ ከፍሎችና በአፍሪካ ሀገራት ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት የተያዘውን ውጥን በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ምርምር ዘርፍ በርካታ ችግር ፈቺ ሥራዎችን የሠራ መሆኑን አንሥተው በቅርቡ በጃፓን ያገኘውን ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ሽልማት ለአብነት ጠቅሰዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለይ ከእንሰት ድኅረ ምረት አሰባሰብና ማቀነባበር ሂደት ጋር የተያያዙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ወደ አርሶ አደሩ ማዳረስ የጀመረ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተክሉ የዚህ ቤተ ሙከራ መቋቋም አርሶ አደሩ ከበሽታ የጸዱ ችግኞችን በብዛት እንዲያገኝ በማድረግ ምርታማነትን የሚያሳድግ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው እንሰት ላይ የሚሠራውን ሥራ የተሟላ የሚያደርግ ነው ብለዋል። በትብበር ፕሮጀክቱ ይፋ የተደረጉ ሥራዎች እንሰትን በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጭምር እንዲሰፉ የሚያደረጉ ናቸው ያሉት ዶ/ር ተክሉ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሠራው ሞባይል መተግበሪያም አርሶ አደሮችም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሥራቸውን በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲሠሩ የሚያስችል መሆኑን አውስተዋል።
የአልባስተር ኢንተርናሽናል መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሻነን ፈርናንዶ ተቋማቸው ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረው ጠንካራ ትብብር የሚታዩ ውጤቶችን እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይፋ የተደረገው የእንሰት ሞባይል መተግበሪያ እንሰት ላይ ያለ ሀገር በቀል ዕውቀትን ዲጂታላይዝ አድርጎ ያቀርባል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ መተግበሪያው ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም እንሰትን የተመለከተ ፈጣን የባለሙያ ምክር መስጠት የሚችል እንደሆነም ተናግረዋል። እንሰት አብቃይ አርሶ አደሮች ከካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሻነን ከዚህ አንጻር የሞባይል መተግበሪያው በእንሰት እርሻ ውስጥ ምን ያህል ካርቦን እንደተጠራቀመ ማስላት የሚችል በመሆኑ አርሶ አደሩ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ይረዳልም ብለዋል፡፡
የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ የቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪ በኮሌጁ ውስጥ ሥራ መጀመሩ ለምርምር እና ፈጠራ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን አመልክተዋል። ላቦራቶሪው ኮሌጁ አርሶ አደሮችን በመደገፍና ምርታማነትን በማሻሻል ረገድ ትልቅ ሚና እንዲጫወት የሚረዳ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 
የትብብር ፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ ፕሮጀክቱ በአምስት የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ትብብር ተግባራዊ እየሆነ የሚገኝ መሆኑን ተናግረው አዲስ የተመሠረተው ላቦራቶሪ የእንሰት ምርታማነትን በእጅጉ እየጎዳና ትልቅ አደጋ አየፈጠረ የሚገኘውን የእንሰት አጠውልግ በሽታን ለመጋፈጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል። የቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪው ከበሽታ ነፃ የሆኑ የእንሰት ችግኞችን በብዛት በማቅረብ የበሽታውን ጫና የሚቀንስ መሆኑንም ዶ/ር ሳቡራ ተናግረዋል። ላቦራቶሪው በዘመናዊ ማሽኖች ጭምር የተደራጀ ሲሆን ይህም ላቦራቶሪውን ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ እንደሚያደርገው ዶ/ር ሳቡራ አክለዋል።
በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ ቡድን መሪ ዶ/ር ገዛኻኝ ጋሮ የእንሰት ሞባይል መተግበሪያ የእንሰት ምርታማነትን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መተግበሪያው በእንሰት አብቃይ ክልሎች ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የሚያግዝ ሲሆን እንሰትን ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት የሚግዝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት አማካሪና በኮሌጁ የዕፅዋት ማዳቀል እና የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር መሠረት ፈንታ የቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪ ከበሽታ የጸዱ የዕፅዋት ችግኞችን /Planting Materials/ በእጅግ ከፍተኛ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማባዛት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ዩኒቨርሲቲ የዚህ ዓይነት ዘመኑን የዋጁ ቤተ ሙከራዎች ባለቤት መሆን መቻል ለተቋሙ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የአልባስተር ኢንተርናሽናል ቡድን አባላት በፕሮጀክቱ ትብብር የሚሠሩ የምርምር መስኮችን፣ በሴቶች የሚመሩ ከእንሰት ቃጫ ጌጣ ጌጦችን የሚያመርቱ ማኅበራትን፣ ዘመናዊ የእንሰት ማቀነባበሪያ ማዕከሎችንና የእናቶች ማቆያዎችን የተመለከቱ ሲሆን በመጨረሻም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና አልባስተር ኢንተርናሽናል በእንሰት ምርምር፣ ፈጠራ እና የማኅበረሰብ ልማት ተግባራትን ለማጠናከር እና ለማስፋት የሚያስችል የተሻሻለ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ተፈራርመዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

