የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርፕርነርሺፕ ልማትና ማበልፀጊያ ማዕከል ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሣምንትን አስመልክቶ ኅዳር 09/2017 ዓ/ም ከሁሉም ካምፓስ ለተወጣጡ ተማሪዎች በሥራ፣ በስኬታማ ኢንተርፕርነር ምንነት፣ በቢዝነስ ሃሳብና ባሕርያት እንዲሁም በተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሣምንት ለ11ኛ ዙር ከኅዳር 09-15/2017 ዓ/ም ሥልጠና በመስጠት፣ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር በማካሄድ እና በፓናል ውይይት የሚከበር ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ለ3ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕርነርሺፕ ልማትና ማበልፀጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ እንደገለጹት ሥልጠናው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሣምንትን በማስመልከት ተማሪዎች ከሚማሩት ትምህርት ጎን ለጎን ሥራ ፈጣሪ የመሆን ፍላጎትና እይታቸው እንዲጨምር እንዲሁም በቂ ግንዛቤ መጨበጥ እንዲችሉ በማለም የተዘጋጀ ነው፡፡ ‹‹ኢንተርፕርነር መሆን ሳይቻል ራስ ገዝ መሆን አይቻልም›› ያሉት ዶ/ር ወንድወሰን የዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ ኢንተርፕርነራል የመሆን ራእይ ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ኅዳር 13/2017 ዓ/ም ዓለም አቀፍ ተጋባዥ እንግዶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላትና ማኅበረሰቡ በተገኙበት የጋራ ምክክር የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው መምህርትና የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት አሠልጣኝ ፍቅርተ ሥዩም በሀገር ደረጃ የተሻለ ኢንተርፕርነር ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን በመጥቀስ በቢዝነስ ዓለም የሚገጥሙ ስጋቶችን በመፍራት ዘርፉን የማይቀላቀሉና የቢዝነስ ሥራ ጀምረው የሚያቋርጡ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ መ/ርት ፍቅርተ አያይዘውም ስኬታማ ኢንተርፕርነር ለመሆን የተሻለ ግብ ማስቀመጥ፣ በቂ ጥናትና ምርምር ማካሄድ፣ መረጃን አነፍንፎ ማግኘትና መጠቀም እንዲሁም አስቀድሞ ሊገጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን መለየት፣ ኃላፊነት መውሰድና መሰል የቢዝነስ ባህርያት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡ ቢዝነስ ሥራ ዕድል ሳይሆን ጥረት የሚጠይቅና በሰዎች የሚመረጥ የተሻለ የቢዝነስ ሃሳብ የሚፈልግ መሆኑን መ/ርት ፍቅርተ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የ2ኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሣይንስ ተማሪ የናትፋንታው ኑሪ እና የ3ኛ ዓመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ዮሐንስ ዓለማየሁ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ሰፋ ባለ መልኩ የቀረበ በመሆኑ በኢንተርፕርነርሽፕ ምንነት ዙሪያ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ከማስቻሉም ባሻገር በቢዝነስ ሥራ መረጃን አፈላልጎ መጠቀምና የሚገጥሙ ስጋቶችን አስቀድሞ አማራጭ መፍትሔ መውሰድ የተሰኙ ባሕሪያት ትኩረታቸውን ከሳቡ ርእሰ ጉዳዮች መካከል እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት