በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት አዘጋጅነት ጥቅምት 26/2017 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ሴት ተመራማሪዎች ማኅበር ምሥረታ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሴት ተመራማሪዎች እርስ በእርሳቸው እንዲመካከሩ፣ መተባበር እንዲችሉና ድጋፍ እንዲጠይቁ እንደ ሀገር ከአንድ ወር በፊት የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር የተመሠረተ ሲሆን ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የየራሳቸውን እንዲመሠርቱ የተቀመጠ አቅጣጫን መሠረት በማድረግ ማኅበሩ በዩኒቨርሲቲው መመስርቱን ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ በምርምር ዳይሬክቶሬት፣ በሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤቱ እና በአምዩ አይዩሲ ፕሮጀክት ትብብር በዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራን የምርምር ተሳትፎ እያደገ እንዲመጣ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተሳትፎውን ይበልጥ ለማሻሻል የሴት ተመራማሪዎች ማኅበሩ የሚመሠረት መሆኑን ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ዶ/ር አዳነች ዘመዴ የኢትዮጵያ ሴት ተመራማሪዎች ማኅበር የመተዳደሪያ ደንብን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በምርምር የሴቶች ተሳትፎ፣ የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር አጀማመርና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲሁም ሴት ተመራማሪዎችን በምርምርና በፈጠራ ማብቃት በሚሉ ነጥቦች ላይ በመምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ጸጋነሽ አንበሴ ገለጻ ተደርጓል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የሴት ተመራማሪዎች ማኅበር ለመመሥረት ከቀረቡ ስምንት ዕጩዎች መካከል ዶ/ር አዳነች ዘመዴ ፕሬዝደንት፣ ዶ/ር ሕይወት ጸጋዬ ም/ፕሬዝደንት፣ ዶ/ር ትዝታ እንዳለ ጸሐፊ፣ ዶ/ር መሠረት ፈንታ ሰነድ ያዥ፣ ዶ/ር ጸጋነሽ አንበሴ ገንዘብ ያዥ እንዲሁም ዶ/ር መቅደስ ኡርጌ እና ዶ/ር እልፍነሽ በርሄ አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡
በጉባኤው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና ጨምሮ ከ6ቱም ካምፓሶች የመጡ ሴት መምህራንና ተመራማሪዎች ታድመዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

