በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጫሞ ካምፓስ ተማሪ የነበረው ተከሳሽ ተማሪ ናሁሰናይ ይታየው ስያምር በተማሪ መኖሪያ ክፍል አብሮ ይኖር የነበረውን ተማሪ ናትናዔል ፅጉን በስለት ወግቶ በመግደሉ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ታኅሣሥ 22/2018 ዓ/ም በዋለው ችሎት የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ወንጀሉ የተፈፀመው ዕለተ ማክሰኞ በቀን 28/08/2017 / በግምት ከጠዋቱ 320 ሰዓት ላይዩኒቨርሲቲው ጫሞ ካምፓስ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የተማሪ ማደሪያ ህንፃ ቁጥር 9 የማደሪያ ክፍል 01 ውስጥ ነበር። በዕለቱ ተከሳሽ ናሁሰናይ ይታየው ስያምር ሟች ተማሪ ናትናዔል ፅጉን በምመገበው ምግብ እና ውሃ ውስጥ ኬሚካል በመጨመር ጉበቴ እንዲበላሽ አድርጓል በሚል ምክንያት አስቀድሞ ቂም በመያዝ በመኝታ ክፍል ውስጥ ሟችን ለመግደል ደብቆ ባስቀመጠው ቢለዋ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ደጋግሞ በመውጋት በአሰቃቂ ሁኔታ ጉዳት በማድረስ ለሞት መዳረጉን ፍርድ ቤቱ በማስረጃ አረጋግጧል። ተከሳሽ ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ ከተማሪ ማደሪያ ክፍሉ በመሸሽ ላይ እያለ በአካባቢው ባሉ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች አማካኝነት የተያዘ ሲሆን ሟች ተማሪ ናትናዔል ፅጉ ወደ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ተወስዶ በሕክምና ላይ እያለ በዕለቱ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

በመሆኑም ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቀድሞ በማሰብ በአካል ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መሳሪያ በመጠቀም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሟችን በመግደል የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀፅ 539 (1-) ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ የከባድ የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኗል፡፡ ተከሳሽ የቅጣት ማቅለያ ሃሳብ እንዲያቀርብ ታዞ ማቅረብ ባለመቻሉ የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል

በዩኒቨርሲቲው የሕግ ባለሙያ አቶ ብሩክ ኩችላ ወንጀሉ ከሰብአዊነት ያፈነገጠ መሆኑንና በዚህም የዩኒቨርሲቲው ሕግ ባለሙያዎችና ጸጥታና ደኅንነት አካላት እንዲሁም ከዞን ፖሊስ መምሪያ ጋር በመተባበር በወንጀሉ ፍትሕ አሰጣጥ ዙሪያ  እየተሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት